የይርጋለም ቁጥር 1 ባለ 132 ኪሎ ቮልት የማከፋፊያ ጣቢያን ለማዘመንና የኦፕሬሽን ሥራውን ለማቀላጠፍ የሚያስችል የመቆጣጠሪያ ወይም ብሬከር ቅየራ እየተከናወነ መሆኑን የጣቢያው ኃላፊ ገለፁ፡፡
ኃላፊው አቶ ፈይሰል ዋቤ እንደገለፁት የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት የማከፋፈያ ጣቢያዉን አቅም የማሳደግና የማሻሻል እንዲሁም መቆጣጠሪያዎችን የማዘመን ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያዉ ሦስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት እና ሦስት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ሲኖሩት ለይርጋለም ከተማና አካባቢው፣ ለይርጋለም ችፑድ ፋብሪካ፣ ለአፖስቶ፣ ለሀንጠጤ፣ ለለኩ ከተማ፣ ሀገረ ሰላም፣ በንሳ ዳዬ እና በዙሪያቸው ላሉ አካባቢዎች ኃይል እያቀረበ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በደቡብ አንድ ሪጅን የማከፋፊያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ ያለው አማረ በበኩላቸው የብሬከር ቅየራው ኃይል ሳይቋረጥ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ቀደም ሲል በሪጅኑ በሚገኙት በሻኪሶና ሻሸመኔ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ባለ 33 ኪሎ ቮልት መቆጣጠሪያዎች ቅየራ መከናወኑን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት በዲላ፣ ሻሸመኔና በይርጋለም ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተመሳሳይ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



