የጣቢያውን ሠራተኞች አቅም ለማሳደግ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው

የጣቢያውን ሠራተኞች አቅም ለማሳደግ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተከዜ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሠራተኞችን አቅም ለመገንባት ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ጣቢያው አስታወቀ።

የጣቢያው የሰው ኃይል፣ ንብረትና ጠቅላላ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን ገ/ሊባኖስ እንደተናገሩት የሠራተኞችን አቅም ለማጎልበት የሥራ ላይ ሥልጠና ከመስጠት ባለፈ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ ጋር ተነጋግሮ መምህራንን ሠራተኞቹ ወዳሉበት ቦታ በማስመደብ የቅዳሜና እሁድ የትምህርት መርሃግብር ተጀምሯል፡፡

ጣቢያው የመምህራንን ማረፊያ፣ የመመላለሻ ትራንስፖርት፣ የመማሪያ ክፍል እና በኃይል ማመንጫ ቤቱና በማከፋፊያ ጣቢያው በተግባር የታገዘ ትምህርት የሚማሩበትን ሁኔታ ማመቻቸቱን ገልጸዋል።

እንደ አቶ መኮንን ገለጻ ጣቢያው ባመቻቸው የትምህርት እድል እስከ አሁን 26 የሚደርሱ ሠራተኞች የተመረቁ ሲሆን 14 የሚሆኑት ደግሞ በትምህርት ላይይገኛሉ፡፡

በጣቢያው የኦፕሬሽንና ጥገና ክፍል ባለሙያ በርኸ ደስታ ሠራተኛው ስራውን እየሰራ አቅሙን የሚያሳድግበትና የእውቀት አድማሱን የሚያሰፋበት ዕድል መፈጠሩ የሚበረታታ መሆኑን ገልጿል።

የጣቢያውን ሥራ በተሻለ ዕውቀት በማከናወን ውጤት ለማስመዝገብ አቅሙ የተገነባ ሠራተኛ መኖሩ አስፈላጊ ነው የሚለው ባለሙያው በቀጣይ ሙሉ የትምህርት ወጪቸውን የሚሸፈንበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቋል።

የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ የሆነው ሌላኛው የጣቢያው ባለሙያ ዮናስ ገብረ ዮሐንስ በበኩሉ የትምህርት ዕድሉ ሙያዊ አቅማቸውን ለማሳደግና የተሻለ ደረጃ ለመድረስ የሚረዳ መሆኑን ተናግሯል።

ቀደም ሲል ሠራተኛው ትምህርት ለመማር ሲል ሥራ ለቆ እስከመሄድ ያስብ ነበር የሚለው ባለሙያው አሁን ግን ሠራተኛው ተረጋግቶ ሳይጉላላ ትምህርቱን እየተማረ መሆኑን ገልጿል።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ሙሴ ኃየሎም ዩኒቨርስቲው የሚሰጠው ትምህርት ተማሪዎቹ በተግባር የሚያውቁትን ዘመኑ ከደረሰበት የእውቀት ደረጃ ጋር አዋህደው እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው ብለዋል።

መቀሌ ዩኒቨርስቲ የጣቢያውን ውጤታማነት ለማሳደግ በሚያስችሉ የሰው ሀብት ልማት ላይ ከጣቢያው ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት መምህር ሙሴ በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ዕድገት ላይ የበኩላችውን አሻራ ለማሳረፍ እድል በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

Scroll to Top