በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የሚፈፀመው ስርቆት አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ በሚከናወነው ሥራ ላይ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱን የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ።
በዘርፉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና የሪጂን ማስተባበሪያ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ መንግስቱ እንደተናገሩት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም ሪጂኖች በሚገኙ የኃይል ማስተላለፈያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ስርቆት ተፈፅሟል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ሽቦ ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ በተፈፀመ ስርቆት 22 ምሰሶዎች መውደቃቸውን እና ከዚህ ውስጥ ሰባቱ በሰሜን ምዕራብ ሪጂን በተፈፀመ ስርቆት የወደቁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
አስር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎችን ፈታትቶ ለመውሰድ በተፈፀመ ከፍተኛ ስርቆት ምክንያት በጊዜያዊነት ኃይል ማስተላለፍ አቋርጠው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በስርቆት ምክንያት ከወደቁ ምስሶዎች በተጨማሪ ከመሬት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዙ እና በሌሎች ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ደግሞ 13 ምሰሶዎች መውደቃቸውንም አስታውቀዋል።
በዘርፉ የሪጂን የኃይል ማስተላለፊያ መስመስና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተሮች እንደገለፁት አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የተለያዩ ሥራዎች አየተከናወኑ ቢሆንም እየተባባሰ የመጣው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች አካላት ስርቆት በኦፕሬሽን ሥራው ላይ ፈተና እየሆነ ይገኛል።
የስርቆት ችግሩ ከመደበኛ ሥራቸው ይልቅ በአስቸኳይ የጥገና ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ እያስገደዳቸው ስለመሆኑም አመልክተዋል።
የስርቆት ወንጀሎችን ቀድሞ ለመከላከል በተቋሙና በሪጂኖች የተለያዩ ሥራዎች ቢከናወኑም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሆኑ ከተቋሙ አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ነው ኃላፊዎቹ ያነሱት።
በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ተቋሙ ከከፍተኛ የመንግስት አካላት ጋር በመወያየት ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ማስቀመጥ ይኖርበታል ብለዋል።
በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች የኃይል መቆራረጥ እንዲያጋጥም ከማድረግ ባለፈ ተቋሙን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረገው ይገኛል።

