የደጀን ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት የፍተሻ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር በፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች አስተባባሪ ገለጹ፡፡
አስተባባሪው አቶ ተስፋሚካኤል አሰፋ እንደገለጹት በግንባታ ላይ የሚገኘው የደጀን የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ 90 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ያላቸው አንድ ባለ 63 እና አንድ ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር ትራንስፎርመሮች አሉት፡፡
አምስት ባለ 33 እና አምስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ያሉት የማከፋፈያ ጣቢያው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ ከ87 በመቶ በላይ እንደተጠናቀቀና በዕቃ አቅርቦት ችግር ምክንያት ያልተከናወኑ ቀሪ ሥራዎች ከፍተሻ ሥራው ጎን ለጎን እንደሚከናወኑም አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡
የጣቢያው የፍተሻ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር ያነሱት አቶ ተስፋሚካኤል የግንባታና የፍተሻ ሥራዎችን በተያዘው የበጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ሲቪል ሥራዎች የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ታምራት በበኩላቸው 83 በመቶ የሚሆነው የስዊችያርድ የሲቪል ግንባታ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን የመኖሪያ ቤት ግንባታን ጨምሮ የማከፋፈያ ጣቢያው አጠቃላይ የሲቪል ሥራ 65 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡
የስዊችያርድ አጥር፣ የውጭ ተፋሰስ፣ የመኖሪያ ቤት ግንባታና የጣቢያው የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ያነሱት ሥራ አስኪያጁ ስዊችያርዱን ጠጠር የማልበስ እና ማከፋፈያ ጣቢያውን ከዋናው መንገድ የሚያገናኝ የ1 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራዎች በቀጣይ እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የደጀን ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የደጀን -ደብረ ማርቆስ የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሥራ 86 በመቶ ላይ መድረሱን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ እንዳለ ላቀው ተናግረዋል፡፡
በመስመሩ ላይ ከሚተከሉ 111 የኃይል ተሸካሚ ምሶሶዎች መካከል የ98ቱ የተከላ እና የ40 ምሶሶዎች የመስመር ዝርጋታ ሥራዎች መከናወናቸውንም አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡
የጸጥታ ስጋት፣ የሲሚንቶና ብረት እጥረት እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች አቅርቦት መዘግየት በፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ላይ ችግር ሆኖ መቆየቱን ያስታወሱት ኃላፊዎቹ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅም ከዕቃ አቅርቦትና ከጸጥታ ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡
የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ፕሮግራም 1 ፕሮጀክት ማኔጅመንት 2 ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ሽኩር በበኩላቸው በፕሮጀክቱ ላይ የተስተዋሉ ችግሮች ፕሮጀክቱ በተያዘለት መርሀ ግብር መሰረት እንዳይጠናቀቅ ማድረጉን ገልፀው ችግሮችን ለመፍታትም የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ እና የብረት እጥረቱ እንደተቀረፈ ያነሱት አቶ መሐመድ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ ቀሪ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች እስከ ግንቦት መጀመሪያ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚቀርቡ በአቅራቢው በኩል ይሁንታ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 87 ነጥብ 5 በመቶ የደረሰ ሲሆን ሥራው ሲጠናቀቅ በደጀን ከተማና በዙሪያው ለሚገኙ ወረዳዎች እና ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ያግዛል፡፡
ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት እየተከናወነ የሚገኘው የደጀን-ደብረ ማርቆስ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት የግንባታ ሥራ በራስ ኃይል መምሪያ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በዕቃ አቅርቦቱ ደግሞ ፓወር ቻይና የተባለ ኩባንያ እየተሳተፈበት ይገኛል፡፡


