ተቋሙ የኢፍጣር መርሃ ግብር አካሄደ

ተቋሙ የኢፍጣር መርሃ ግብር አካሄደ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የረመዳን ፆምን ምክንያት በማድረግ የእስልምና እምነት ተከታይ ለሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች፣ ደንበኞች እና ባለድርሻ አካላት በስካይ ላይት ሆቴል የኢፍጣር ወይም የእራት ግብዣ መርሃ ግብር አካሄደ።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በአንድነት የእራት ግብዣ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የረመዳን ጾም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሥጋዊ ፍላጎትን በመንፈሣዊ ፅናት በማሸነፍ ራሱን ለፈጣሪ ማስገዛት የህይወት መመሪያው የሚያደርግበት ወር መሆኑን አንስተዋል።

የተዘጋጀው መርሃግብር እንደ ኢትዮጵያውያን ወግና ባህል ማዕድን በጋራ በመቋደስ ስለስኬቶቻችን፣ ስለወደፊት መዳረሻዎቻችን እና ስለፈተናዎቻችን ለመነጋገር ታስቦ መሆኑን ሥራ አስፈፃሚው ጠቅሰዋል።

ከአምስቱ የእስልምና እምነት መሠረቶች መካከል አንዱ የሆነው ፆም የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ከአላህ እዝነት ለማግኘት ትልቅ ጥረት የሚደረግበት እንደሆነም ነው የገለፁት።

ተቋሙ በህዝብና በመንግሥት የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ከምንጊዜውም በላይ እየሰራ ነው ያሉት ሥራ አስፈፃሚው የህዝቡን፣ የደንበኞችንና የሀገርን ፍላጎት ማርካት የሚያስችሉ ዕቅዶች አዘጋጅቶ በትግበራ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ስለሆነም የተቋሙን ራዕይ ለማሳካት ሁሉም የተቋሙ ሠራተኛ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ለእስልምና እምነት ተከታዮችም ለ1445ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

በኢፍጣር መርሃግብሩ ላይ የታደሙት የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች በበኩላቸው በዝግጅቱ መደሰታቸውንና የእኔነት ስሜት እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።

እንደዚህ ዓይነት መርሃ ግብሮች በቀጣይም ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በማንሳት ለተደረገላቸው የአንድነት የእራት ግብዣ ተቋሙንና ዋና ሥራ አስፈፃሚውን አመስግነዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢ/ር አሸብር ባልቻን ጨምሮ የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ ደንበኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

Scroll to Top