የሦስት ተርባይኖችን የጥገና ሥራ ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም ተከናውኗል

የሦስት ተርባይኖችን የጥገና ሥራ ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም ተከናውኗል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ካሉት አራት ተርባይኖች የሦስቱን ጥገና ሥራ ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም ማከናወን ጣቢያው አስታወቀ።

በጣቢያው የጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ስዩም ኃይሉ እንደገለጹት ከ2013 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለተወሰኑ ወራት የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ከብሔራዊ የኃይል ቋት ውጪ ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል።

ይሁንና አካባቢው ወደ ሠላም ከተመለሰ በኋላ ጣቢያው ካሉት አራት ተርባይኖች ውስጥ የሦስቱን ተርባይኖች ጥገና ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም መከናወኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

እንደ አቶ ስዩም ገለፃ ቀሪው ተርባይን ተፈቶ የጥገና ሥራ እየተከናወነ ነው።

ጥገናቸው ከተጠናቀቁት ሦስት ተርባይኖች መካከል አንዱ በንዝረት ፍተሻ ላይ በመሆኑ በአሁን ወቅት ጣቢያው በሁለት ተርባይኖች ኤሌክትሪክ እያመነጨ ይገኛል ብለዋል።

ጣቢያው በሙሉ አቅሙ ኃይል ወደ ማመንጨት እንዲገባ የሚያስችሉ የማስተካከያ፣ የቅድመ መከላከል የጥገና ሥራዎች እንዲሁም ሳምንታዊና ወርሃዊ የፍተሻ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

የጣቢያው የጥገና ባለሙያ የሆኑት አቶ ሚካኤለ ገብረ ጻዲቅ በበኩላቸው የተርባይንን ጨምሮ ሌሎች የጥገና ሥራዎችን በራስ አቅም እያከናወኑ በመሆናቸው ጊዜንና ወጭን መቆጠብ እንዳስቻለ ተናግረዋል።

የጣቢያውን የጥገና ሥራዎች በራስ አቅም ማከናወናቸው ሠራተኞች እርስ በእርስ ልምድ የሚለዋወጡበትና አቅማቸውን የሚያጎለብቱበትን እድል እንደፈጠረላቸውም ጠቁመዋል።

ከመለዋወጫ ዕቃ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈታላቸውም ጠይቀዋል።

በ1994 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ ጥቅምት 2002 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 300 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው።

Scroll to Top