
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጠንካራ የሥራ ባህል እና ጽናት የታየበት እንደሆነ የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ የጣሊያኑ ዊ ቢውልድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፔትሮ ሳሊኒ ተናገሩ፡፡
ሥራ አስፈጻሚው በግድቡ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ የግድብ ግንባታው ተጠናቆ ሲታይ ቀላል ቢመስልም በርካታ ፈተናዎችን እና ውጣ ውረዶችን በጽናት ማለፉን ተናግረዋል፡፡
ግድቡ አሁን ላይ የሚያስፈልገውን ውሃ መያዙን እና የሀገሪቱን የማመንጨት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ በርካታ ኢትዮጵያውያን የኃይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤቶቿ በመሸጥ ትብብሯን ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አስገንዝበዋል::
የህዳሴ ግድብ በዓለማችን ደህንነታቸው ከተጠበቁ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚው በግንባታው ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በጽናትና በቁርጠኝነት የተሳተፉበት እንዲሁም የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ያገኙበት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የግድብ ግንባታው መጠናቀቅ የኔ እና የኢትዮጵያ ህልም እውን የሆነበት ነውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በፈተናዎችና በችግሮች ሳይበገሩ ግድቡ እንዲጠናቀቅ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን የጠቆሙት ፔትሮ ሳሊኒ ለግድብ ግንባታው እውን መሆን አሻራቸውን ላሳረፉ ሠራተኞችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በግድቡ ግንባታ ሥራ ላይ እየተሳተፉ በነበረበት ወቅት በተለያዩ አደጋዎች ሕይወታቸውን ላጡ ሠራተኞች ክብር እንደሚሰጡ እና በኅሊና እንደሚያስቧቸው ተናግረዋል።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ለመንግሥታቸው የላኩትን የደስታ መግለጫ መልዕክትም አቅርበዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”