የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለምርቃት ዝግጁ መሆን ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ያለመጨረስ የባሕል ልምምድ ላይ የተሰነዘረ መዶሻ መሆኑን የአፍሪካ ሥራ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ ተናገሩ።
ፕሬዚደንቱ ይህን የተናገሩት ለሕዳሴ ግድብ ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች እና ባለሙያዎች በሰጡት ስልጠና ላይ ነው።
እንደ አቶ ዛዲግ ገለጻ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፉክክርን ወደ ትብብር በመቀየር ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመፈጸም ሀገራዊ መሰረት የተጣለበት እንዲሁም ብሔራዊ ማንነታችንንና የፍላጎታችንን አዋጅ የተነገረበት ነጋሪት ጋዜጣ ነው።
የግድብ ግንባታው የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ ቦንድ የገዛውና ገንዘብ የለገሰው ሕዝብ በወቅቱ ይታየው የነበረው የመሰረት ድንጋይ ሳይሆን የመነጨ የኤሌክትሪክ ኃይል እና ብርሃን ነበር ብለዋል።
ሕዝቡ ከመንግስት ጋር በመተባበር በጨለማ እየኖረ በቅርብ ላላየው ብርሃን ታጋይ ሆኖ የዘመኑ አደዋ የሆነውን የሕዳሴ ግድብ ግንባታን የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ እንዲደርስ ማድረጉን ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ መጠናቀቅ የአባይ ምንጭ የነበረችዋን ኢትዮጵያ 5 ሺ 150 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል እንድትሆን መደላድል የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ አቶ ዛዲግ ገለፃ ግድቡ አፍሪካ ያላትን ፀጋ በራሷ ልጆች ዕውቀት፣ ጉልበትና ገንዘብ ወደ ሀብት በመቀየር መልማት እንደምትችል ለዓለም ያሳየ የአደባባይ ትዕምርት ነው።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
