ከእንጦጦ ፓርክ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የኤሌክትሪክ ገመዶችን በመቁረጥ የሰረቁ ተከሳሾች እስከ 23 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ፡፡
መልካሙ ማቴዎስ፣ ቢኒያም ካሳሁን፣ ደረጄ ተሰማ፣ ቶፊቅ ዓለሙ፣ አማኑኤል አቡ፣ አስመላሽ ትዕግስቱ እና ዓለሙ ተመስገን የተባሉ ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱን የፈፀሙት ጥቅምት 4 ቀን 2016 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው እንጦጦ ፓርክ ውስጥ ነው።
ተከሳሾች አባሪ ተባባሪ በመሆን ለእንጦጦ ፓርክ አገልግሎት እንዲውል የተዘረጋ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ ቆርጠው በኮድ1 ላዳ ተሽከርካሪ ጭነው ለመውሰድ ሲሉ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ሲካሄድባቸው ቆይቷል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ያጠናቀረውን የምርመራ መዝገብ አቃቤህግ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ የወንጀል ጉዳዮች ችሎት አቅርቧል፡፡
ፖሊስ በምርመራ መዝገቡ ተከሳሾቹ በተለያዩ ጊዜያት በሌሊት እንጦጦ ፓርክ ግቢ ውስጥ በመግባት የተዘረጉ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመዶችን እየቆረጡ በተሽከርካሪ በመጫን ሰርቀው በመውሰድና ሸጠው በመከፋፈል ተግባር መሰማራታቸውን ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱም እንደ ወንጀሉ አፈፃፀምና ተሳትፏቸው መጠን ተከሳሾችን ያስተምራል፣ ሌሎች ወንጀል ፈፃሚዎችን ያስጠነቅቃል ሲል ከ6 ዓመት ከ9 ወር እስከ 23 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፍርድ ውሳኔ ሰጥቶባቸዋል።
የመረጃ ምንጫችን የአዲስ አበባ ፖሊስ ነው።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”