በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ጉዳት የደረሰበትን የኮምቦልቻ- አላማጣ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ ሁለተኛ ሰርኪዩት መስመር ኃይል ሳይቋረጥ በአዲስ የኮንዳክተር ገመድ የመቀየር ሥራ ሙሉ በመሉ መጠናቀቁን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ቢዝነስ አስታወቀ።
በትራንስሚሽን ቢዝነስ የፕሮጀክት ማኔጂመንት 1 ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ሙሉ ብርሃን እንዳስታወቁት 114 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ከኮምቦልቻ- አላማጣ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ሁለተኛ ሰርኪዩት የኮንዳክተር ሽቦ ዝርጋታ ሥራ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የመስመሩ መጠናቀቅ በኮምቦልቻ እና አላማጣ እንዲሁም አጎራባች ከተሞች በኤሌክትሪክ መቋረጥ ሳቢያ ሊፈጠር የሚችለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማስቀረት የጎላ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታው ከ2013 ዓ.ም በፊት ተጠናቆ ለፍተሻና ሙከራ ሥራ ዝግጁ እንደነበር ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ በወቅቱ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት መስመሩ መጎዳቱን ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ አሸናፊ ገለፃ ከዚህ በፊት ከለገጣፎ- ኮምቦልቻ 61 ኪሎ ሜትር የኃይል ማሰተላለፊያ መስመር የኮንዳክተር ገመድ ቅየራ ሥራ ተጠናቆ ለህብረተሰቡ ያልተቆራረጠ ኃይል ማቅረብ መጀመሩንም አስታውሰዋል።
ከለገጣፎ- ኮምቦልቻ በተከናወነው የኮንዳክተር ገመድ ቅየራ ሥራ ከመስመሩ ኃይል ለሚያገኙ አካባቢዎች እና ለለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲሁም ለደብረ-ብርሃን ኢንዱስትሪ ዞን አስተማማኝ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ማስቻሉንም ነው የጠቀሱት።
በአንድ ዓመት ውስጥ የተጠናቀቀው የኮንዳክተር ገመድ ቅየራ ሥራ የግሪድ ሥርዓቱን ከማረጋጋት ባሻገር ተጨማሪ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ማስቻሉንም ነው ያስረዱት።
የመስመር ዝርጋታ ሥራውን ኃይል ሳይቋረጥ ማከናወን መቻሉ ለተቋሙ ትልቅ እምርታ መሆኑን ያብራሩት አቶ አሸናፊ ሥራው በተቋሙ የኮንስትራክሽን ማኔጂመንት መምሪያ ሠራተኞች አቅም በስኬት በመጠናቀቁ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
