ሠራተኛው ለተቋማዊ ስኬት በእኔነት ስሜት ሊሰራ ይገባል  –  ዶ/ር አብርሃም በላይ

ሠራተኛው ለተቋማዊ ስኬት በእኔነት ስሜት ሊሰራ ይገባል  –  ዶ/ር አብርሃም በላይ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሠራተኛ ለተቋማዊ ስኬት በእኔነት ስሜት ሊሰራ እንደሚገባ የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አሳሰቡ።

‎የቦርድ ሰብሳቢው ዶ/ር አብርሃም በላይ እንደገለጹት በሀገሪቱ እያደገ ላለው የኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ተጨማሪ የኃይል መሰረተ ልማቶችን በከፍተኛ ፍጥነትና አቅም መገንባት ያስፈልጋል።

‌‎ሀገሪቱ ኃይል ለማመንጨት ያላትን እምቅ አቅም በጥናት ላይ ተመስርቶ ወደ ተግባር በመለወጥ የኃይል አማራጮችን ለማስፋት እና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ተቋሙ ጊዜን ቀድሞ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ዶ/ር አብርሃም እንደገለፁት የመነጨውን ኃይል ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ አስተማማኝ የግሪድ መሰረተ ልማት ከመዘርጋት ጀምሮ ነባሮቹን በማሻሻልና በማዘመን ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አንስተዋል።

‎ለዚህም ተቋሙ የሚያስተዳድረውን ከፍተኛ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት አሰራሮቹን ማዘመንና የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን ማጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

መንግስት የተቋሙን የፋይናንስ ቁመና ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ እርምጃዎችን መውሰዱን በማስታወስ ቀጣይነት ያለው ለውጥ በማምጣት ተቋሙን ውጤታማ ለማድረግ በመንግስት በሚወሰዱ እርምጃዎች ሳይዘናጉ አቅዶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች የሚቀርበው ኃይል በአሰራር የተደገፈ ባለመሆኑ በአቅርቦቱ ላይ የተለያዩ ችግሮች እንደነበሩበት የተናገሩት ዶ/ር አብረሃም ችግሮቹን የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት መፍትሔ እስኪሰጠው ድረስ ተጨማሪ የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶችን ማስተናገድ መታገዱን ገልፀዋል።

በዚህም የዳታ ማይኒንግ የኃይል አቅርቦትን ተጠያቂነትና ግልፅነት ባለው መልኩ በማድረግ ሀገሪቱ በአግባቡ ገቢ እንድታገኝ ለማስቻል በጥናት ላይ የተመሰረተ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ከፕሮጀክቶች አፈፃፀም፣ የተቋሙን ገፅታ ከመገንባትና ሥራዎቹን ከማስተዋወቅ፣ ከሴቶች ተሳትፎ እና ተቋማዊ አቅምን ከመገንባት አንፃር ያሉ ክፍተቶችን በፍጥነት ማረም እንደሚገባም አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

በሠራተኞች የተነሱ ጥያቄዎችንና ትኩረት እንዲሰጣቸው የቀረቡ ጉዳዮችን በዕቅድ አካቶ መስራት እንደሚገባ የገለፁት ዶ/ር አብርሃም ሠራተኛውን ሊያሰራ የሚችል አደረጃጀት እና ምቹ የሥራ ሁኔታ መኖሩን ለማረጋገጥ የሥራ አመራር ቦርዱ የሚያደርገውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የተቋሙ የሥራ መሪና ሠራተኛም ራሱን በእውቀትና በሥነ-ምግባር በማሳደግ፣ ሀገርንና ተቋምን በማስቀደም በእኔነት ስሜት በኃይል ዘርፉ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ሊያከናውን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡‎

‎የሠራተኛ ማህበር ተወካይና የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ተሾመ በላይ በበኩላቸው የሠራተኛውን መብትና ጥቅም፣ የሙያ ደህንነትና ጤንነት እንዲሁም የሥራ ዋስትና እንዲረጋገጥ እና የኢንዱስትሪ ሠላም እንዲሰፍን ቦርዱ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ተቋሙ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚጫወተውን አውንታዊ ሚና ከግምት በማስገባት ሠራተኛው በሙሉ አቅሙ መስራት አለበት ያሉት አቶ ተሾመ የሠራተኛውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በዕቅድ ተይዘው እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top