የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2017 በጀት ዓመት በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ ገለጹ።
የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ከመ/ቤቱ የሥራ መሪዎች እና ሠራተኞች ጋር በተቋሙ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት እያደረገ ነው።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ በተቋሙ የ2017 በጀት ዓመት በኃይል ማመንጨትና ማስተላለፍ፣ በኃይል ሽያጭ፣ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ በሠው ኃይል ልማት እና በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሁም ተቋሙ እያካሄደ ባለው ሪፎርም ዙሪያ የተከናወኑ ሥራዎችን አቀርበዋል።
በበጀት ዓመቱ ለሀገር ውስጥና ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኃይል ሽያጭ ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከሦስት እጥፍ በላይ ያለው ገቢ መገኘቱንም ጠቁመዋል።
ይህ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው ያረጁ መስመሮችን በመቀየር፣ የጥገናና የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማዘመን፣ የውዝፍ ገቢ አሰባሰቡን በማጠናከር፣ የገቢ አማራጮችን በማስፋት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ተርባይኖች ወደ ኦፕሬሽን በማስገባት እና የታሪፍ ማሻሻያ በመደረጉ ነው ብለዋል።
ሆኖም በፕሮጀክት አስተዳደር፣ በተለያዩ ወሳኝ የሙያ መስኮች የበቁ ባለሙያዎችን አለማፍራት፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮችን በተሟላ መልኩ አለመተግበር እና በመልሶ ግንባታ ላይ ፈጣን ሥራዎችን ከመስራት አንጻር ክፍተቶች መታየታቸውን አንስተዋል።
ኢንጅነር አሸብር አክለውም ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ስርቆት፣ ከካሳ ክፈያ ጥያቄዎችና በአንዳንደ አካባቢዎች የነበሩ የፀጥታ ችግሮች በበጀት ዓመቱ የገጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸው አብራርተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማጎልበትና ክፍተቶችን በማረም እንዲሁም ጠንካራ የፕሮጀክት ክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ይሰራል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ለካፒታል ወጭዎች፣ ለመደበኛ በጀት እንዲሁም ለወለድ ክፍያ 251 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተያዘ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከዚህ ውስጥ ከ55 በመቶ በላይ የሚሆነውን ከተቋሙ የኃይል ሽያጭና ልዩ ልዩ ገቢዎች ለመሸፈን መታቀዱን ተናግረዋል።
ሕዳሴ እና አሰላ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገቡ የተናገሩት ኢንጅነር አሸብር ቀሪ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በማሻሻልና ብክነትን በመቀነስ በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ለዚህም የቦርዱ ሁለንተናዊ ድጋፍ፣ የተቋሙ ሠራተኛና አመራር ቅንጅታዊ አሰራሩን በማሳደግ ለዕቅዱ ስኬት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በቀረበው ሪፖርት ላይ ሠራተኞች ጥያቄዎችና አስተያየቶችን እያቀረቡ ይገኛል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



