የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበጀት ዓመቱ የሴቶችን የአመራር ሰጪነት ሚና ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከፓዎር አካዳሚ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የምክክር መድረክ ሲከፍቱ እንደተናገሩት የሴቶችን የአመራር ሰጪነት ሚና የማሳደግ ሥራ በአመራሩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
ሴቶች በባለሙያነትም ሆነ በኃላፊነት በተመደቡበት ቦታ ሁሉ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢትዮ ፓዎር አካዳሚ ዳይሬክተር ወንድወሰን ካሳ ( ዶ/ር) የተቋሙን የሴቶች አቅም እና የአመራር ሰጭነት ሚና ለማሳደግ በሚያስችሉ ሀገራዊ እና ዓለምቀፋዊ አሰራሮች ላይ ያተኮረ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
ምንም እንኳን ሴቶች በአመራር ሰጭነት እና በተቋማዊ የሥራ አፈፃፀም ክንውን ጉልህ ድርሻ ቢኖራቸውም በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ተሳትፏቸው አነስተኛ መሆኑ በቀረበው ጽሁፍ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሴቶችን ተሳታፊ የሚያደረግ ፖሊሲ እና የአሰራር ማዕቀፎችን ቀርፆ ቢንቀሳቀስም ተሳትፎአቸው ከ18 በመቶ እንዳልዘለለ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በተቋሙ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ በበኩላቸው ሴቶችን ለማብቃት እና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የተቋሙ የሥራ መሪዎች ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
ሴቶችም ተጠቃሚነታቸውን እና ተሳትፎኣቸውን ለማሳደግ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ መካከለኛ እና የበላይ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን ሴቶች ለራሳቸው እና ሌሎች ለሴቶች የሚሰጡት የተሳሳተ ግምት እንዲሁም ሴቶችን ማዕከል ያላደረጉ ፖሊሲ እና የሥራ አካባቢዎች እንዲስተካከሉ፤ ለሴቶች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በልዩ ሁኔታ እንዲዘጋጁ፣ የሴቶችን ተጠቃሚነት እና አካታችነት የሚያረጋግጡ አስራሮች ተግባራዊ እንዲደረጉ ጠይቀዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




