የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ ለኃይል ማመንጫ ግድቦች ደህንነት መጠበቅ ሚናው የጎላ ነው

የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ ለኃይል ማመንጫ ግድቦች ደህንነት መጠበቅ ሚናው የጎላ ነው

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተቋሙን የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ የጎላ ሚና እንዳለው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፓወር ግሪድ ኦፕሬሽን መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች ዛሬ የችግኝ ተከላ ሲያከናውኑ የመምሪያው ዳይሬክተር ኢንጂነር ሚኪያስ ወንድሙ እንደገለጹት በየዓመቱ እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ግድቦችን ከደለል በመከላከል ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል ነው።

መርሀ ግብሩ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ እንዲኖር በማድረግ ተቋሙ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም አስተማማኝና ዘላቂ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማቅረብ የያዘውን ተልዕኮ ለማሳካት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የመምሪያው ሠራተኞች የተከሏቸውን ችግኞች በእኔነት ስሜት በመንከባከብ የመጽደቅ ምጣኔያቸውን ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በችግኝ ተከላው ላይ የተገኙት የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሱራፌል ቢያብል በበኩላቸው በወረዳው በሚገኘው የተቋሙ ግቢ ውስጥ ችግኞች በመተከላቸውና ወረዳውም ተሳታፊ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

‎መርሀ ግብሩ አካባቢውን ፅዱና አረንጓዴ ከማድረጉ በተጨማሪ እየተተከሉ የሚገኙ ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ በመሆኑ የምግብ ዋስትናዋን ያረጋገጠች ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

‎በቀጣይም በአረንጓዴ ልማት አሻራ መርሀ ግብሩና በሌሎች ጉዳዮች አስተዳደሩ ከተቋሙ ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top