የኤሌክትሪክ ግሪድ ማለት ኤሌክትሪክን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያደርሱ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ብቻ አይደለም። የኃይል ማመንጫዎች፣ ማስተላለፊያ መስመሮች፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ ትራንስፎርመሮችና የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎች በሙሉ የአንድ ግሪድ አካላት ናቸው። ይህ መሠረተ ልማት በአካላዊ ጉዳት ከተጎዳ የኃይል አቅርቦት ሊቋረጥ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴም ሊጎዳ ይችላል።
የግሪድ አካላዊ ደህንነት ማለት እነዚህን የኃይል መሠረተ ልማቶች ከስርቆት፣ ከብልሽት፣ ያልተፈቀደለት ሰው መሳሪያዎቹ ወደሚገኙበት ከመግባትና ከሌሎች አካላዊ ጥቃቶች መጠበቅ ማለት ነው። በዓለም አቀፍ የኃይል ዘርፍ ውስጥ የግሪድ አካላዊ ደህንነትን ማስጠበቅ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስተማማኝነት ከሚያረጋግጡ ዋና ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል።
🛡️ እያንዳንዱን የኃይል መሠረተ ልማት በሰው ጥበቃ ብቻ ማስጠበቅ ይቻላል?
መልሱ አይቻልም ነው።
የኤሌክትሪክ ግሪድ በጠባብ መልክዓ ምድር የተወሰነ አይደለም። በመሆኑም ሁሉም የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ፣ መስመርና መሠረተ ልማት ባለበት ቦታ የጥበቃ ሠራተኛ ማቆም ተግባራዊም ሆነ ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም። ስለዚህ የዘመኑ የደህንነት ውጤት የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ የሰው ኃይልንና የማህበረሰብ ትብብርን በማቀናጀት መስራት ያስፈልጋል።
📹 ዘመናዊ ካሜራና የክትትል ሥርዓት
የCCTV ካሜራዎች፣ የመግቢያ ቁጥጥር፣ የማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችና ሌሎች የክትትል ቴክኖሎጂዎች አጠራጣሪ እንቅስቃሴን በፍጥነት ለመለየትና ምላሽ ለመስጠት ይረዳሉ። ይህ ሥርዓት የሰዎች ጥበቃን በካሜራ ለመተካት ሳይሆን የሰው ኃይልን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ነው።
🤝 ማህበረሰቡ የግሪድ ጥበቃ አካል ነው!
የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች በብዙ ማህበረሰቦች መንደር ያልፋሉ። ጋራና ሸንተረሩን ያቋርጣሉ፡፡ ስለሆነም ማስተላለፊያ መስመሩ በሚያልፍባቸው አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች አጠራጣሪ የሰዎች እንቅስቃሴ፣ የመሠረተ ልማት ስርቆት ሙከራ ወይም ሌላ አደገኛ ሁኔታ ሲመለከቱ በራሳቸው ጉዳዩን ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በአቅራቢያቸው ለሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላት ወይም ለሚመለከተው ተቋም ማሳወቅ ይገባዋል።
ይህ የመሠረተ ልማቱን ደህንነት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የራሳችንን ህይወትና ደህንነት መጠበቅም ጭምር ነው።
⚡ የኤሌክትሪክ ግሪድ ደህንነት = የኃይል አስተማማኝነት + የኢኮኖሚ ቀጣይነት + የሀገር ደህንነት
የኤሌክትሪክ ኃይል ለጤና ተቋማት፣ ለፋብሪካዎች፣ ለትምህርት፣ ለቴክኖሎጂ፣ ለንግድና ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሠረት ነው። ስለዚህ የኃይል መሠረተ ልማትን መጠበቅ የአንድ ተቋም ብቻ ኃላፊነት ሳይሆን የመንግሥት ተቋማት፣ የሕግ አስከባሪ አካላትና የማህበረሰቡ የጋራ ኃላፊነት ነው። የግሪድ ደህንነት በተቋማት መካከል ቅንጅትንና ቀጣይ ክትትልን ይፈልጋል።
🔒 የኃይል መሠረተ ልማት የጋራ ሀብታችን ነው። እንጠብቀው!