የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው የፋብሪካውን የማምረት አቅም በእጥፍ አሳድጓል

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው የፋብሪካውን የማምረት አቅም በእጥፍ አሳድጓል

​የጉደር ባለ 132 ኪሎ ቮልት ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በአካባቢው ለሚገኙ ፋብሪካዎች አስተማማኝ ኃይል በማቅረብ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የአምቦ ውኃ ፋብሪካ አስታወቀ።

​የፋብሪካው የማኑፋክቸሪንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈለቀ ተስፋዬ እንደገለፁት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ለአምቦ ውኃ ፋብሪካና በአካባቢው ለሚገኙ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

​ፋብሪካው ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የኃይል አቅርቦት እጥረት ዋነኛ ፈተና እንደነበር የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያው በመተከሉ የፋብሪካውን የማምረት አቅም በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

​ከዚህ ቀደም ያጋጥም በነበረው የኃይል መቆራረጥ ምክንያት ፋብሪካው ለከፍተኛ የምርት ብክነት እና ለገንዘብ ኪሳራ ይዳረግ እንደነበርም አብራርተዋል።

​እንደ አቶ ፈለቀ ገለፃ በአሁኑ ወቅት የኃይል መቋረጡ በመቀረፉ ፋብሪካው ቀደም ሲል በቀን በአማካኝ ያመርተው ከነበረው 12 ሺህ ሣጥን የምርት መጠን አሁን ላይ ወደ 25 ሺህ ሣጥን ማሳደግ ተችሏል።

​ይህ የምርት ዕድገት በፋብሪካው አካባቢ ለሚገኙ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ በተለይም ከቋሚ ሠራተኞች ውጭ በማህበር ለተደራጁ ከ50 በላይ ወጣቶች በምርት ጭነት፣ ማውረድ እና ድርደራ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ ማስቻሉን ተናግረዋል።

​ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት አስተማማኝና በቂ ኃይል እያገኘ በመሆኑ የማምረት አቅሙን የበለጠ በማሳደግ ተጨማሪ የሰው ኃይል ለመቅጠር ማቀዱንም ገልፀዋል።

Scroll to Top