በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሥራ ቦታ የሚታዩ የሥነ-ምግባር ጉድለቶችን በማረም ተቋማዊ ግቦችን ለማሳካትና የአፈጻጸም ክፍተቶችን ለመድፈን የሠራተኞችን የመፈጸም አቅም የሚያጎልብቱ ተከታታይ ስልጠናዎች ወሳኝ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ተወካይ ኃላፊ ግርማ ግዛቸው (ዶ/ር) «የሠራተኞች ተሳትፎ ለተቋማዊ ዕድገት» በሚል መሪ ቃል ሲሰጥ በቆየው አራተኛው ዙር ስልጠና ሲጠናቀቅ ባስተላለፉት መልዕክት ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ያስመዘገባቸው በርካታ ስኬቶች ቢኖሩትም በፕሮጀክት አመራር፣ በሠራተኛ ተሳትፎ፣ በሀብት አጠቃቀም እና ንብረት አስተዳደር በኩል ክፍተቶች እንደነበሩ ገልፀዋል።

በመሆኑም የተዘጋጀው ስልጠና የሠራተኛውን የመፈጸም አቅም በማጎልበት የተቋሙን ግቦች ለማሳካት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በመረዳትና «ተቋሙ ካልኖረ እኔም አልኖርም» የሚል አስተሳሰብ በመያዝ የተቋሙን ገጽታና ስትራቴጂ በሚገባ ተረድቶ መስራት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
የተቋሙ የኮርፖሬት ገቨርናንስና ኮምፕሊያንስ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዱጉማ ነዳ በበኩላቸው ተቋሙ በየጊዜው በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ስልጠናዎች የሚገኙ እውቀቶችን መሬት ላይ ማውረድና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሥራ ቦታ የሚታዩ የሥነ-ምግባር ጉድለቶች ለተቋማዊ ዕድገት አደገኛ በመሆናቸው ችግሮቹን ለማረም ቁርጠኝነትን የሚጠይቅና ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በመጥቀስ አመራሩ በሥነ-ምግባርና በአሠራር ደንቦች መከበር ላይ ለሠራተኛው አርአያ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
የተቋሙ የሰው ኃይል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አታላይ አበበ ተቋሙ ቀጣይነት ያለውና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሰው ኃይል አደረጃጀት ለመዘርጋት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲሱ የሰው ኃይል አስተዳደር ሥርዓት በሥነ-ምግባርና በብቃት ላይ የተመሠረተ የሠራተኞች ዕድገትና የምልመላ ሥራዎችን ማዕከል ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ለሠራተኞች የሚሰጡ የሥራ ዕድገቶችና የተለያዩ ዕድሎች ብቃትንና ሥነ-ምግባርን መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው ሠራተኛው ራሱን ማብቃትና ማሻሻል እንዳለበትመም ነው ያስገነዘቡት።





