የኤሌክትሪክ ፍላጎት ከተሞች በሚያድጉበት፣ ኢንዱስትሪዎች በሚስፋፉበትና አዳዲስ የንግድ እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በሚቋቋሙበት ፍጥነት እየጨመረ ነው። ይህንን እያደገ የመጣ ፍላጎት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስተናገድ የማከፋፈያ ጣቢያዎች አቅም ማሳደግና የማስፋፊያ ሥራዎች ወሳኝ ናቸው።
🏗️ የአቅም ማሻሻያና ማስፋፊያ ሥራ ምን ያካትታል?
የማከፋፈያ ጣቢያ አቅም ማሻሻያ ማለት የኃይል ፍላጎቱን በመገምገም ተጨማሪ የትራንስፎርመሮችን አቅም መጨመር፣ ያረጁ ወይም የአቅም ውስንነት የገጠማቸውን መሳሪያዎች በሌላ መተካት፣ አዳዲስ ፊደሮችን (feeders) መጨመር፣ የመከላከያና የቁጥጥር ሥርዓቶችን ማዘመን፣ ኬብሎችንና ሌሎች የማከፋፈያ ጣቢያ የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎችን አቅም ማሳደግ እና አዲስ ጣቢያ መገንባትን ያካትታል።
📈 የአቅም ማሻሻያና ማስፋፊያ ሥራ ለምን ያስፈልጋል?
የከተማ ህዝብ ቁጥር ሲጨምር፣ አዳዲስ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ማዕከላት ሲገነቡ፣ ፋብሪካዎች ሲስፋፉ እና አዳዲስ የኃይል ተጠቃሚዎች ሲጨምሩ በጣቢያዎች ላይ የሚጫነው የኃይል ጭነትም ይጨምራል። አቅሙ ያልተሻሻለ ጣቢያ ይህንን የጭነት ዕድገት ለማስተናገድ ሲቸገር የመሣሪያ መጫን ከአቅም በላይ ሊሆን ብልሽትና የኃይል መቆራረጥ ሊጨምር ይችላል። የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የኃይል ዘርፍ ግምገማ ይህንን ችግር በተለይ በከተሞች ያሉ የማከፋፈያ ኔትወርኮች ከፍላጎት ዕድገት ጋር በበቂ ሁኔታ እንዳልተስማሙ ጠቁሟል።
🔌 1. የኃይል እጥረትን ለመቀነስ
የማከፋፈያ ጣቢያዎች የማስፋፊያ ሥራ ተጨማሪ የማመንጨት አቅም ሳይሆን የተመነጨውን ኃይል በበቂ አቅምና በተሻለ አስተማማኝነት ወደ ተጠቃሚዎች ለማድረስ የሚያስችል የግሪድ አቅም ማሳደግ ነው፡፡ በመሆኑም አዲስ ትራንስፎርመሮች፣ ፊደሮች እና የማስተላለፊያ/ማከፋፈያ መሣሪያዎች ሲጨመሩ የጣቢያው ጭነት ሸክም ይቀላል፣ ኃይልን የማስተላለፍ አቅም ይጨምራል፣ የመቆራረጥ ስጋትም ሊቀንስ ይችላል።
🏭 2. ለኢንዱስትሪና ለከተማ ኢኮኖሚ አስተማማኝ ግብዓት ለመሆን
በቂና አስተማማኝ ኃይል ለፋብሪካዎች፣ ለንግድ ተቋማት፣ ለሆስፒታሎች፣ ለትምህርት ተቋማት፣ ለቴክኖሎጂ እና ለሌሎች የከተማ አገልግሎቶች የማይተካ ግብዓት ነው። የማከፋፈያ አቅም ሲሻሻል አዳዲስ ተጠቃሚዎችን ለማገናኘት ተጨማሪ አቅም ይፈጠራል፤ የንግድና የፋብሪካ ምርት ሥራዎችም በተሻለ የኃይል አቅርቦት ሊከናወኑ ይችላሉ። በኢትዮጵያ የማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅም ማሻሻያ ፕሮጀክቶች የሚተገበረው አቅምን ከማሳደግ ባለፈ የአቅርቦት ተዓማኒነትን ለማሻሻል ነው።
⚙️ 3. ማስፋፊያ ማለት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ መዘጋጀት ስለሆነ
የከተሞች ዕድገትና የኢንዱስትሪ መስፋፋት ሲፋጠን የኃይል ፍላጎትም አብሮ ይጨምራል። ስለዚህ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም አሁን ካለው ፍላጎት በመነሳት ብቻ ሳይሆን የወደፊት የኃይል ፍላጎት ዕድገትን በመተንበይ ማሻሻልና ማስፋፋት የኃይል ሥርዓቱን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ወሳኝ ነው።
🇪🇹 የማከፋፈያ ጣቢያ አቅም ማሻሻያ ማለት የተሻለ የኃይል አቅርቦት፣ የተሻለ አስተማማኝነት፣ የተሻለ የከተማ እድገትና የተሻለ ኢኮኖሚ ማለት ነው።
⚡ የኃይል ግሪድ ሲሰፋና ሲጠናከር፣ ከተሞች ያድጋሉ፣ ኢንዱስትሪዎች ይስፋፋሉ፣ ኢኮኖሚውም ይንቀሳቀሳል።