በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደሴ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ በተያዘለት መርሃግብር እየተከናወነ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ተናገሩ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ዳንኤል ተክለማርያም እንደተናገሩት ተቋሙ ሁለት 63 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮች እንዲሁም 6 ባለ 33 ኪሎ ቮልት እና 10 ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ያሉት የማከፋፈያ ጣቢያ በደሴ ከተማ እየገነባ ይገኛል፡፡



1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር አጠቃላይ በጀት ተይዞለት እየተገነባ ያለውን ፕሮጀክት በተቋሙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የራስ ኃይል ግንባታ መምሪያ እያከናወነው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ግንባታውን እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2019 ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ዳንኤል የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ሲጠናቀቅ ለደሴ ከተማ እና ለአከባቢው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል፡፡



በአሁኑ ወቅት ትራንስፎርመሮችን በቦታቸው የማስቀመጥ ሥራ ተከናውኖ ለመቆጣጠሪያ ክፍል ህንፃ ግንባታ የሚሆን የመሬት ቆረጣ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ የደሴ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ከፍተኛ የመሬት ቆረጣ የሚፈልግ በመሆኑ የቆረጣ ሥራዉን በፍጥነት ለማከናወን ተጨማሪ ማሽነሪዎችን ወደ ሳይት ለማስገባት ታቅዷል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለደሴ ከተማና አካባቢው የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት የመስተዳድር አካላት እና ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ለ94 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመው ሥራው እየሰፋ ሲሄድ ተጨማሪ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንደሚያሳትፍ ተናግረዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




