የሽግዳን ባለ 230/132/33 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እና ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት የሰላማጎ ወረዳና የአካባቢው ነዋሪዎችን የዘመናት የኤሌክትሪክ ኃይል ጥያቄ እንደሚመልስ የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የወረዳው አስተዳዳሪ ዋና አማካሪ አቶ ስምዖን ኤርሚያስ እንደገለፁት የሰላማጎ ወረዳ መቀመጫ በሆነችው ሐና ሙርሲ ከተማ ጨምሮ በወረዳው ሥር የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ባለመሆናቸው በአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ ባለሀብቶች በአካባቢዉ ከማልማት ይልቅ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሸሹ እያደረጋቸው እንደሆነና መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፈቃድ የወሰዱ ባለሃብቶችም ወደ ሥራ አለመግባታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
የሽግዳን ማከፋፈያ ጣቢያ እና ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ግንባታ ከተጀመረ ወዲህ ባለሃብቶች በአካባቢው ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለፁት አማካሪው ይህም በቀጣይ አካባቢውን የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃ አመልክተዋል።
እንደ አማካሪው ገለፃ የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ለወረዳው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባለፈ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶችን አደራጅቶ በተለያዩ ዘርፎች ለማሰማራት ያግዛል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ በመፋጠን ላይ የሚገኝ ሲሆን በሥራው ላይ ችግር እንዳያጋጥም መስመሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች አደረጃጀት በመፍጠርና በወረዳ ደረጃም አራት የቴክኒክ ቡድኖችን በማዋቀር ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ማህበረሰቡን እስከ አሁን ከነበረበት ጨለማ የሚያወጣ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪ እና ወረዳዉ ለፕሮጀክቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አማካሪው አረጋግጠዋል፡፡
የሰላማጎ ወረዳ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ስር ከሚገኙ ስድስት ወረዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን የወረዳው መቀመጫ የሆነችው ሐና ሙርሲ ከተማም ከአዲስ አበባ በ880 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”