የገናሌ ዳዋ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ የዞንና የወረዳ መስተዳድር አካላት የጣቢያውን ጥብቅ ወሰን የማስከበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥሪ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች፣ የኦሮሚያ ክልል የልማት ተነሺ እና የውሃ ሀብት ቢሮ አመራሮች እንዲሁም የዞንና የወረዳ መስተዳድር አካላት በገናሌ ዳዋ የውሃ ኃይል ማመንጫ የጥብቅ ወሰን ወይም በፈር ዞን የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
በተቋሙ የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት፣ ክትትልና ቁጥጥር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ በመስክ ምልከታው ወቅት እንደገለጹት የጣቢያውንና የማህበረሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ጥብቅ ወሰን በመከለል ተቋሙ ከቦታው ለተነሱ ሰዎች ካሳ ከፍሏል፡፡
ሆኖም ተቋሙ ካሳ ክፍሏቸው እስከ አሁን ከጥብቅ ወሰኑ ያልተነሱ የልማት ተነሽዎች ከመኖራቸው በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችም ወሰኑን አልፈው እርሻ በማረስ በግድቡ ደህንነትና በኦፕሬሽን ሥራው ላይ አደጋ መደቀናቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ ዋለ አክለውም በግድቡ ወሰን ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በክረምት ወራት ለጎርፍ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
ይህም የማህበረሰቡን ደህንነት ለአደጋ በማጋለጥ ተቋሙን ለአላስፈላጊ የካሳ ጥያቄ እንደሚዳርገው ነው የተናገሩት።
በጣቢያው ጥብቅ ወሰን ውስጥ ሆነው ካሳ ሳይከፈላቸው የቀሩ ሰዎች ካሉ ተቋሙ በትክክለኛ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዋለ የዞንና የወረዳ የመስተዳድር አካላት ግድቡ ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ከግምት በማስገባት የጣቢያውን ጥብቅ ወሰን የማስከበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የልማት ተነሺዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ተስፋ በበኩላቸው የግድቡ ውሃ በሚተኛበት ዙሪያ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች በግድቡና በአካባቢው ማህበረሰብ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ሥጋት መደቀናቸውን ተናግረዋል፡፡
የዞንና የወረዳ የመስተዳድር አካላት ከጣቢያው ወሰን ውስጥ የሰፈሩ የልማት ተነሺዎችን አማራጭ ቦታ በማዘጋጀት ወሰኑን ማስጠበቅ እንዳለባቸው ያሳሰቡት አቶ አለማየሁ ከካሳ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች ካሉም በቀጣይ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው እንደሚመለሱ ገልጸዋል፡፡
የነገሌ ቦረና ከተማ የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ከግድቡ ጥብቅ ወሰን ውስጥ በመሰራቱ በክረምት ወራት የግድቡ ወኃ ሲሞላ በፓምፖቹ እና የውኃ መግቢያ (intake) ላይ ጫና እንደሚፈጥር በመስክ ምልከታቸው ማረጋገጣቸውንም አብራርተዋል፡፡
ይህም በአካባቢው የንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ገልጸው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የውኃ ፕሮጀክቱን ከጥብቅ ወሰኑ ውጭ የቦታ ቅያሬ (Relocate) ለማድረግ በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ተቋሙ ካሳ በከፈለበት የጣቢያው ጥብቅ ወሰን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለማግኘት ላቀረበው ጥያቄም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከመስተዳድር አካላት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።
ጉጅና ባሌ ዞንን የሚያስተሳስረው የገናሌ ዳዋ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን 254 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አለው።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



