የአዲጋላ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለፁት የአዲጋላ ማከፋፈያ ጣቢያ የኤክስፖርት ጣቢያ ከመሆኑ ባለፈ ወደ ጅቡቲ ለተዘረጋው የውሃ መስመር አስተማማኝ ኤሌክትሪክ እያቀረበ ይገኛል።
ተቋሙ ለሚያከናውነው የኃይል ሽያጭ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ለተመሰረተው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ መድረስ ጣቢያው አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲጋላ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ሳሙኤል በበኩላቸው ማከፋፈያ ጣቢያው የተገነባው ኢትዮጵያ በምስራቁ በኩል ከጎረቤት ጅቡቲ ጋር ለሚኖራት የኃይል ኤክስፖርት ማሳለጫ ታስቦ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው 25 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያለው አንድ ትራንስፎርመር እና 74 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው አራት ሪአክተሮች እንዲሁም በ33 ኪሎ ቮልት አምስት ወጪ መስመሮች እንዳሉት አቶ ዮናስ ጠቁመዋል፡፡
ወጪ መስመሮቹም ለአዲጋላ፣ ለአይሻ፣ ለደወሌ እና ለአርዌ ከተሞች እንዲሁም ለኢትዮ- ጅቡቲ የባቡር እና ለጅቡቲ የውሃ መስመሮች አስተማማኝ ኤሌክትሪክ እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በጣቢያው የሚገኙት አራቱ ሪአክተሮች የቮልቴጅ መዋዠቅ ችግር እንዳይፈጠር በማድረግ የተመጠነ እና ያልተቆራረጠ ኃይል እንዲቀርብ ያስችላል።
በአካባቢው በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚፈፀም ስርቆት አለመኖሩን የገለፁት አቶ ዮናስ ህብረተሰቡ መሰረተ ልማቶቹን በጋራ ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ ባህል እንዳለውም ተናግረዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



