በበዓሉ የነበረው ከፍተኛው የኃይል ጭነት 3 ሺ 884 ሜጋ ዋት ሆኖ ተመዝግቧል

በበዓሉ የነበረው ከፍተኛው የኃይል ጭነት 3 ሺ 884 ሜጋ ዋት ሆኖ ተመዝግቧል

በትላንትናው ዕለት በተከበረው የ2017 ዓ.ም የገና በዓል 3 ሺ 884 ሜጋ ዋት ኃይል መመዝገቡን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል አስታወቀ።

የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ሚኪያስ ወንድሙ እንዳስታወቁት ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በበዓሉ ዕለት የኃይል መቋረጥ እንዳያጋጥም ከኃይል ማመንጫ እስከ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ ነበር።

ለበዓሉ እና ለዋዜማው 4 ሺ 750 ሜጋ ዋት ኃይል ዝግጁ መደረጉንና በዋዜማው 4 ሺ 309 ሜጋ ዋት እንዲሁም በበዓሉ ዕለት 3 ሺ 884 ሜጋ ዋት ኃይል መመዝገቡን ነው ያስታወቁት።

ይህም ለማቅረብ ከተዘጋጀው ውስጥ በዋዜማው 441 ሜጋ ዋት እንዲሁም በበዓሉ ዕለት 866 ሜጋ ዋት ትርፍ ኃይል እንደነበር አቶ ሚኪያስ ተናግረዋል።

በዋዜማው የተመዘገበው ኃይል ከ2016 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር በ787 ሜጋ ዋት ወይም የ22 በመቶ እንዲሁም የበዓሉ ዕለት በ1 ሺ 196 ሜጋ ዋት ወይም የ44 በመቶ ብልጫ ያለው መሆንኑ ጠቅሰዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ከመንዲ- አሶሳ በተዘረጋው መስመር ላይ በበዓሉ ዋዜማ ምሽት ባጋጠመ ችግር ምክንያት ከተቋረጠ ኃይል ውጭ በሌሎች መስመሮች፣ በማመንጫ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ምንም ዓይነት ችግር ስላልተከሰተ ኃይል አልተቋረጠም።

በመስመሩ በተተከሉ ስድስት የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ ምሶሶዎች ላይ ባጋጠመ ስርቆት ምክንያት በበዓሉ ዋዜማ ከምሽት ጀምሮ ኃይል መቋረጡን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ የሪጂኑ የጥገና ባለሙያዎች በበዓሉ ዕለት ጉዳት የደረሰባቸውን የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች በመጠገን ከቀኑ 9 ሠዓት ጀምሮ የተቋረጠውን ኃይል መልሶ ማገናኘት ተችሏል ብለዋል።

በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ የኃይል እጥረት ባለማጋጠሙ ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች እና ጎረቤት ሀገራት ጭምር ኃይል ከዚህ በፊት ይቀርብ በነበረው አግባብ እንደተስተናገዱ አንስተዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top