
የኃይል ማመንጫ ግድቦችን በክረምት ወራት ሊፈጠር ከሚችል የጎርፍ አደጋ ለመጠበቅ የዕይታ ፍተሻ እና የግድብ ደህንነት መከታተያ መሳሪያዎችን በመጠቀም ክትትል እየተደረገ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ገለጸ፡፡
በዘርፉ የግድብ ክትትልና ቁጥጥር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ደላሽ እንደገለጹት ክትትሉ የሚከናወነው በክረምት ወራትሊፈጠር ከሚችል የጎርፍ አደጋና የአፈር መንሸራተት ግድቦችን በመጠበቅ የግድቦችን ደህንነት ለማረጋገጥ ነው፡፡
በክረምት ወራት ሊኖር የሚችለው ዝናብ ለኃይል ማመንጫ ግድቦች አስፈላጊ ቢሆንም ከመጠን ሲያልፍ ግን የግድቦችን ደህንነት ስጋት ላይ ሊጥል ስለሚችል በተቋሙ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን የአሠራር መመሪያ መሠረት በከፍተኛ ጥንቃቄ ያልተቋረጠ ክትትል ይደረግበታል ብለዋል፡፡
የግድቦቹን የውሃ ማስተንፈሻ /Spillways/ እና መቆጣጠሪያ በሮች በመጠገንና ለሥራ ብቁ እንዲሆኑ በማድረግ የግድብና ተያያዥ ክፍሎች ላይ ዘወትር የክትትል ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
የግድብ ክትትልና ቁጥጥር ሥራው በየጣቢያዎቹ ኃላፊዎችና ኦፕሬተሮች፣ በየጣቢያው ባሉ የግድብ ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያዎች እና ከዋና መስሪያ ቤት በሚላኩ ባለሙያዎች እንደሚከናወን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ኤሊያስ ገለፃ የሚከናወነው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ከግድቡ በታች የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ከጎርፍ ከመከላከል ባለፈ የግድቦችን ደህንነት በመጠበቅ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ የሚጠበቅባቸውን ኃይል በአግባቡ እንዲያመርቱ ለማድረግ ያግዛል፡፡
የግድብ ክትትልና ቁጥጥር ሥራ ከግድቦቹ ዲዛይን ጀምሮ በግንባታ ሂደት፣ ግድቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ውሃ መያዝ ሲጀምር እና አገልግሎት እየሰጠ ባለበት ሰዓት ጭምር የሚከናወን ነው፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”