ባለፉት አስራ አንድ ወራት ከቀረቡ ቅሬታዎች ለ71  መፍትሔ መሰጠቱ ተገለፀ

ባለፉት አስራ አንድ ወራት ከቀረቡ ቅሬታዎች ለ71  መፍትሔ መሰጠቱ ተገለፀ

ባለፉት አሰራ አንድ ወራት በተቋሙ ሠራተኞችና ደንበኞች ከቀረቡ 135 የተለያዩ የአስተዳደራዊ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች መካከል ለ71ዱ መፍትሔ መሠጠቱን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት አስታወቀ።

በጽ/ቤቱ የአስተዳደራዊ ጉዳዮችና ዶክመንቴሽን ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ እንዳስታወቁት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 81 በመቶ የሚሆነው ከውጭ ደንበኞች 19 በመቶው ደግሞ ከውስጥ ሠራተኞች የቀረቡ  ናቸው።

ከቀረቡ ቅሬታዎች 45ቱ ከተቋሙ  መመሪያና ደንብ እንዲሁም ከተሰጠው ስልጣን ውጭ በመሆናቸው ውድቅ መደረጋቸውን እና  71 ጉዳዮች መፍትሔ እንደተሰጣቸው እንዲሁም 19ኙ በሂደት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የአስተዳደራዊ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች በካሳ ክፍያ፣ በጨረታና ግዥ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት፣ በደረጃ ዕድገትና ዝውውር፣ በጥቅማ ጥቅም እና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ያተኩሩ መሆናቸውንም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ዋለ ገለፃ ከሠራተኞች የሚቀርቡ ቅሬታዎች አመራሮችና ሠራተኞች የህብረት ስምምነቱን ድንጋጌዎች በአግባቡ ባለመረዳትና በራሳቸው ፍላጎት በመተርጎም  የሚመነጩ ናቸው።

ለቅሬታዎች በወቅቱ መፍትሔ ለመስጠት ቅሬታው ከተነሳበት የሥራ ክፍል ጋር በመነጋገር  ከመስራት ባለፈ ጊዜያዊ ኮሚቴ በማዋቀር የሚሰራበት አግባብ እንዳለም አቶ ዋለ አንስተዋል።

ቢሮው ከሠራተኞችና ቅሬታ ከቀረበበት የሥራ ክፍል አመራር ጋር ተቀራርቦ በመሥራቱ በተቋሙ  ላይ የሚቀርቡ አስተዳደራዊ ቅሬታዎች እየቀነሱ መምጣታቸውን አንስተዋል።

አግባብ ያልሆኑ ቅሬታዎችን በማቅረብ ጊዜን ከማባከን ለመዳን እና የሠራተኛውንና የተቋሙን ጥቅም ለማስጠበቅ ሁሉም ተቋሙ የሚተዳደርባቸውን ደንቦችና መመሪያዎች ጠንቅቆ በማወቅ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ከካሳ ክፍያና ከኃይል ተደራሽነት ጋር በተያያዘ ከውጭ ደንበኞች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ እንደሆነም አቶ ዋለ ተናግረዋል።

የካሳ ክፍያ ቅሬታዎች አብዛኞቹ ከኦሮሚያ ክልል እንደሚቀርቡ ያነሱት ሥራ አስኪያጁ ለተቋሙ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመቀነስ የቅሬታዎች አግባብነት በክልሉ የልማት ተነሽዎች ኤጄንሲ በኩል ተጣርቶ ወደ ተቋሙ የሚመጣበት አሰራር መዘርጋቱንም አስታውቀዋል።

ሁሉም ቅሬታዎች ቀጥታ ለተቋሙ ይቀርቡ በነበረበት ጊዜ አግባብነት ያላቸው ቅሬታዎችን በወቅቱ ለመፍታት በሚከናወነው ሥራ ላይ ጫና ፈጥሮ መቆየቱን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

ማከፉፈያ ጣቢያዎች በሚገነቡበት አካባቢ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር  የ40/60 ቀመር አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ ቢሆንም ተቋሙ ማከፉፈያ ጣቢያዎች ከሚገኙበት በምን ያህል ሬዲየስ ውስጥ በገንዘብ ማገዝ እንዳለበት የተቀመጠ ግልጽ አሰራር ባለመኖሩ የቅሬታ ምንጭ እየሆነ መጥቷል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል የአሰራር ሥርዓት ማኑዋል እየተዘጋጀ መሆኑንም አቶ ዋለ ጠቁመዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top