ተቋማቱ ባለፈውን አንድ ዓመት የነበረውን የትብብር ስራ ገመገሙ

ተቋማቱ ባለፈውን አንድ ዓመት የነበረውን የትብብር ስራ ገመገሙ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ለአንድ ዓመት የሠራቸውን የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አፈጻጸም የሁለቱ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች በተገኙበት ገምግመዋል።

የፕሮግራሞቹን አፈጻጸም ያቀረቡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እና የኢቢሲ የክፍያ ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ኤሊያስ አማረ ናቸው።

ከየካቲት 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተቋሙ እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ለማስተዋወቅ ከኢቢሲ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል ውል  ተፈርሞ ሥራ መጀመሩን አቶ ሞገስ ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት በየሳምንቱ በአማርኛና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች በብሔራዊ ሬዲዬና ቴሌቪዥን ጣቢያ የ30 ደቂቃ ፍጆታ ያላቸው ፕሮግራሞች እየተዘጋጁ ሲተላለፉ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተላለፉት ፕሮግራሞች ላይ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ድህረ ፕሮዳክሽን የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ያቀረቡት አቶ ሞገስ በቀጣይ ግን የተሰሩ ፕሮግራሞች ያመጡት ለውጥ በጋራ ሊጠና እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደ ሀገር ብሔራዊ ኩራት እንዲሰማን የሚያደርጉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የሚገነባና ለሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ የሆነ ተቋም ነው።

በመሆኑም ከኢቢሲ ጋር የተጀመረው ሥራ የተቋሙን ዋንኛ ተግባራት ለማስተዋወቅ፣ ከስርቆት፣ ከካሳ ክፍያና ወሰን ማስከበር ጋር እያጋጠሙት ባሉት ችግሮች ዙሪያ ግልጽነት በመፍጠር ህብረተሰቡን ለማሳተፍ ያለመ እንደነበር አንስተዋል።

እንደ አቶ አሸብር ገለጻ ተቋሙን ከማስተዋወቅ አንጻር ባለፈው አንድ ዓመት በተላለፉ ፕሮግራሞች የነበሩ ድክመቶች ታርመው በቀጣይ መርህን ባከበረ መልኩ የተሻሉ ፕሮግራሞችን አብሮ ለመስራት ውይይቱ ማስፈለጉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ ኢቢሲ አብሮ የመስራትና የማገዝ ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡

በውል ከምንገባቸው ፕሮግራሞች ባለፈ ተቀሙን በዜናና በሌሎች አማራጮች ሽፋን ለመስጠት አቅደው እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በእስከአሁን ሂደት የነበሩ ጥንካሬዎችን በማጎልበትና ክፍተቶችን በማረም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በተሻለ መንገድ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top