ተቋሙ ከኢቢሲ ጋር የነበረውን የሥራ ግንኙነት የሚያድስ ስምምነት ተፈራረመ

ተቋሙ ከኢቢሲ ጋር የነበረውን የሥራ ግንኙነት የሚያድስ ስምምነት ተፈራረመ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን ለህብረተሰቡ የበለጠ ለማስተዋወቅ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ ለመስራት ተስማማ፡፡

ስምምነቱ ተቋሙ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን በዜና፣ በመደበኛ ፕሮግራሞች እና በዶኩመንታሪ ዝግጅት እንዲሁም በአጫጭር መልዕክቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ቀደም ሲል የነበረውን ስምምነት ለማደስ መሆኑ በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ እና የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ተፈራርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በፊርማ ስነ-ሥነሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት የተፈረመው ስምምነት በሁለቱ ተቋማት መካከል የነበረውን የሥራ ግንኙነት ለማጠናከር እና ካለፈው ተሞክሮ በመውሰድ የበለጠ ሥራ ለመሥራት ያግዛል።

ሥምምነቱ ተቋሙ እያከናወናቸው ያሉ የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታዎችን በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ቻናሎች እንዲሁም በኢቢሲ ዲጂታል ሚዲያ ለህብረተሰቡ በማድረስ የተቋሙን መልካም ገጽታ ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አንጋፋ የኃይል አቅራቢ ተቋም በመሆኑ በህግ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በህብረተሰቡ ዘንድ የበለጠ እንዲታወቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ተቋሙ ቀፈም ሲል ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ሲሠራቸው የነበሩ የገፅታ ግንባታ ሥራዎች ተቋሙን በማስተዋወቅ  ረገድ ለውጥ ማሳየት ጀምረዋል።

ይሁንና ተቋሙን እየፈተኑት የሚገኙት የካሳ ክፍያ፣ የወሰን ማስከበር እና የኃይል መሠረተ ልማት ስርቆት ለህብረተሰቡ አስተማማኝ ኃይል እንዳይቀርብ ከማድረጋቸውም ባሻገር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ጫና እያሳደሩ በመሆኑን በስፋት ሊሰራባቸው እነወደሚገባ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የተቋሙን ብራንድ በማስተዋወቅ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መካከል ያለውን ልዩነት ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ ለማድረግ እንዲሰራ ሥራ አስፈፃሚው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ በበኩላቸዉ የተደረገው ስምምነት ሁለቱ ተቋማት የጀመሩትን የትብብር ሥራ ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን የሚገነባ ተቋም መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ሚዲያ በተቋም ገፅታ ግንባታ ሥራ ውስጥ የሚኖረውን ፋይዳ በመረዳት ተቋሙ እየሰራ ያለውን ሥራ በብሔራዊ ሚዲያው ለማስተዋወቅ ኢቢሲን በመምረጡ  ደስተኛ ነን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለሀገር እሴት የሚጨምሩና ለዕድገት ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶችን በማስተዋወቅ በመሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ህብረተሰቡ እንዲከላከልና እንዲጠብቅ የማስገንዘብ ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

ተቋማቸው ሀገሪቱ በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት የምታደርገውን እንቅስቃሴ እና ወደፊት የያዘችውን ዕቅድ ለማህበረሰቡ የማሳወቅ ሥራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የኮሙዩኒኬሽን ሥራ ውጤት በሂደት የሚታይ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ተቋማቸው ይሠራል ብለዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top