የውስጥ ኮሙዩኒኬሽንን በማጠናከር በሠራተኛው ዘንድ የእኔነት ስሜትን ለመፍጠር ይሰራል

የውስጥ ኮሙዩኒኬሽንን በማጠናከር በሠራተኛው ዘንድ የእኔነት ስሜትን ለመፍጠር ይሰራል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውስጥ ኮሙኒኬሽን ሥራዎችን በማጠናከር በተቋሙ ሠራተኞች ዘንድ የእኔነት ስሜትን ለማጎልበት እየተሠራ መሆኑን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መመሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት ሠራተኞች ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በውል ተገንዝበው በእኔነት ስሜት ለተቋማዊ ስኬት እንዲሰሩ የሚያደርጉ የውስጥ ኮሙዩኒኬሽን ሥራዎችን በዕቅድ እየተከናወኑ ነው።

በተቋሙ ውስጥ ባሉ የኤሌክትሮኒክስ ማሳያ ቦርዶች፣ በውስጥ ሕትመቶችና በአጭር መልዕክት ማስተላለፊያ ነፃ የተቋሙ ቁጥር አማካኝነት የተቋሙን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ እና ለሠራተኞች በቂ ግንዛቤ የሚፈጥሩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የሥራ ክፍሎች አፈጻጸማቸውን የሚያጎለብቱበት፣ በአንድ ሥራ ሂደት የሚመዘገብ የሠራተኛ ውጤት ለአጠቃላይ ተቋማዊ ስኬትና ለውጥ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ግንዛቤ የሚያገኙበት እና የሥራ ክፍሎች ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች እርስ በእርስ ልምድ የሚወስዱበት አሰራር እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ከሥራ ክብደቱ ጋር ተያይዞ የዘገባ ድግግሞሹ ካልተለያየ በስተቀር ሁሉም የሥራ ክፍሎች የዘገባ ሽፋን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች እንዲሁም በማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በራስ አቅም እየተከናወኑ ያሉ ትልልቅ የጥገና ሥራዎችን ሽፋን እንዲያገኙ እየተደረጉ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሞገስ ይሄም ከተቋም ባሻገር እንደ ሀገር ያለውን ጠቀሜታ በማህበረሰቡና በባለድርሻ አካላት ዘንድ እንዲታወቅ በማድረግ የተቋሙን ገጽታ የመገንባት ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በቀጣይም በሠራተኛው ዘንድ የሚነሱ ችግሮች የሚፈቱባቸው፣ ስለተቋሙ ይበልጥ የሚገነዘቡባቸው እና የእኔነት ስሜትን የሚፈጥሩ መድረኮችን ለመፍጠር መታቀዱን አቶ ሞገስ ገልጸዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top