በማከፋፈያ ጣቢያው ለአካባቢው የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ሥራዎች ሊከናወኑ ነው

በማከፋፈያ ጣቢያው ለአካባቢው የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ሥራዎች ሊከናወኑ ነው

የዲላ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን አቅም ለማሳደግና የማሻሻያ ሥራዎችን ለማከናወን እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ዘካሪያስ መኩሪያ እንደገለፁት ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ በሚገኘው የማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ሊከናወኑ የታቀዱት የአቅም ማሳደግ ሥራዎች ለዲላ ከተማና አካባቢው የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው፡፡

ማከፋፈያ ጣቢያው 12 ሜጋ ዋት ኃይል የመሸከም አቅም ያለው አንድ ባለ 25 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር እንዲሁም ሁለት ባለ 33 ኪሎ ቮልት እና ሦስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች እንዳሉት ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ጣቢያው ከይርጋለም ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ተቀብሎ በአምስቱ የ33 እና 15 ኪሎ ቮልት መስመሮች ለዲላ፣ ጎሎልቻ፣ ጓንጓ፣ ይርጋጨፌ፣ ሱሉሞ፣ ቡሌና ቀባዶ እንዲሁም ወናጎ ከተሞች ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ አቶ ዘካሪያስ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በአሁኑ ወቅት ማከፋፈያ ጣቢያው በ15 ኪሎ ቮልት መስመሮች ለአዳዲስ ደንበኞች ተጨማሪ ኃይል ለማቅረብ አቅም የለውም።

ይህን ተከትሎ በጣቢያው የአቅም ማሳደግና ማሻሻያ ሥራዎችን ለማከናወን እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ነው ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት።

በማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ማስተባበሪያ አንድ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ጌታሁን እንደገለፁት የጣቢያውን አቅም ለማሳደግ የዘመናዊ ስዊች ጊር ገጠማ እንዲሁም ነባሩን ትራንስፎርመር የመቀየር ሥራ ይሰራል።

የአቅም ማሻሻያ ሥራው በዋናነት በ15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ላይ እንደሚከናወን ያነሱት አቶ ፀጋዬ ይህም የጣቢያውን የኦፕሬሽን ሥራዎች ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ ለማዘመን እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

የ15 ኪሎ ቮልት የጂ.አይ.ኤስ ስዊች ጊር ዕቃዎች ተጓጉዘው ጣቢያው ላይ መድረሳቸውንና በቀጣይም የሲቪል፣ የጊዜያዊ መቆጣጠሪያ ክፍልና የገጠማ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጨምረው ገልፀዋል።

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያውን የኦፕሬሽን አቅም ለማሳደግ ተጨማሪ ባለ 30 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንፎርመር በጣቢያው ለማስቀመጥ ዕቅድ መያዙንም ነው አቶ ፀጋዬ የተናገሩት።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top