በበጀት ዓመቱ በ25 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራዎች ይከናወናሉ

በበጀት ዓመቱ በ25 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራዎች ይከናወናሉ

በ2017 በጀት ዓመት በ25 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅም ማሳደግና ማሻሻያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ፡፡

በዘርፉ በሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ማስተባበሪያ አንድ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ጌታሁን እንደገለፁት በሦስት ዓመት ውስጥ የ75 ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል።

የአቅም ማሳደግና የማሻሻያ ሥራው በማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩትን መቆጣጠሪያዎች በሌላ ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ በመቀየር አቅማቸውን ለማሳደግ ያለመ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

የአቅም ማሳደግና ማሻሻያ ሥራው በ2016 በጀት ዓመት እንደተጀመረ የገለፁት አቶ ፀጋዬ በበጀት ዓመቱ በ25 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ሦስት ወራት በጋሸና፣ ድሬዳዋና ጌዶ እንዲሁም አሸጎዳ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ በተቋሙ ባለሙያዎች በተከናወነው ሥራ ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን አስታውቀዋል።

በቀጣይም በደቡብ አንድ ሪጅን ስር በሚገኙት የዲላ፣ ሻሸመኔ እና ይርጋለም ቁጥር አንድ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ተመሳሳይ ሥራዎችን ለማከናወን እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

ተቋሙ የአቅም ማሳደግና ማሻሻያ ሥራዎችን በራሱ ለማከናወን ከሁሉም ሪጅኖች የተውጣጡ 20 ባለሙያዎች በውጭ ሀገር ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ፀጋዬ ገለፃ በጣቢያዎቹ እየተከናወነ የሚገኘው የማሻሻያ ሥራ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን የኦፕሬሽን አቅም ለማሳደግና ለማዘመን የሚያግዝ ነው።

የዘመናዊ መቆጣጠሪያ ወይም ስዊችጊር ገጠማ በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ እየተከናወነ መሆኑ በ15 እና 33 ኪሎ ቮልት መስመሮች በሚከሰቱ ተደጋጋሚ ችግሮች ሳቢያ ይፈጠር የነበረውን የኃይል መቆራረጥና የጥገና ጊዜን ለመቀነስ አወንታዊ ሚና እንዳላቸውም ነው ሥራ አስኪያጁ የገለፁት።

በአሁኑ ወቅት ለ50 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚሆኑ ዘመናዊ የጂ.አይ.ኤስ ስዊችጊር ዕቃዎች መረከባቸውን የጠቀሱት አቶ ፀጋዬ ቀሪ 25 ስዊችጊሮች በምርት ሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም የማሳደግ ሥራው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከዓለም ባንክ እና ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 24 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ወጪ እየተከናወነ ይገኛል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top