በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የደቡብ አንድ ሪጅን የኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ለሦስት የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ የመምሪያው ዳይሬክተር አስታወቁ።
ዳይሬክተሩ አቶ ምትኩ ንጉሴ እንደገለፁት ሪጅኑ በአሁኑ ወቅት ሁዋን ዩ፣ አሲክ እና ፊንጋቺ ለተባሉ ሦስት የዳታ የምናባዊ ግብይት ማቀላጠፊያ ማዕከላት ከ145 በላይ ሜጋ ዋት ኃይል እያቀረበ ይገኛል።
ሁለቱ ኩባንያዎች ከሀዋሳ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ 105 ሜጋ ዋት እንዲሁም አንዱ ኩባንያ ደግሞ ከይርጋለም ቁጥር ማከፋፈያ ጣቢያ 40 ሜጋ ዋት ኃይል እያገኙ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
የዳታ ማይኒንግ ማዕከላቱ የጀመሯቸውን ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ሲያጠናቀቁ ከ270 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት።
በሪጅኑ የሚገኙ አስራ ሁለቱ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች 1 ሺህ 910 ሜጋ ዋት ኃይል የመጫን አቅም ያላቸው መሆኑን ተናግረው በአሁኑ ሰዓት 1 ሺህ 710 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባሳለፍነው በጀት ዓመት ለዳታ ማይኒንግ ማዕከላት ካቀረበው ኃይል ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን መዘገባችን አይዘነጋም።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





