የታወር ስርቆትን ለመከላከል መገናኛ ብዙኃን ህብረተሰቡን በማንቃት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

የታወር ስርቆትን ለመከላከል መገናኛ ብዙኃን ህብረተሰቡን በማንቃት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶችን በዘላቂነት ለመከላከል የመገናኛ ብዙኃን ህብረተሰቡን በማንቃት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥሪ አቀረበ፡፡

የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት ተቋሙ የኃይል መሰረተ ልማቶችን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋፋት በሚያከናውነው ሥራ ላይ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ስርቆት ዋነኛ ፈተና ሆኖበታል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በየደረጃው ከሚገኙ የክልል የመስተዳድርና የጸጥታ አካላት እንዲሁም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ሞገስ ገለፃ ችግሩ በሚጎላባቸው አካባቢዎች ከሚካሄዱት የምክክር መድረኮች በተጨማሪ ተቋሙ በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እና በሌሎችም የኮሙዩኒኬሽን አማራጮች ግንዛቤ ለመፍጠር እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ይሁንና ከችግሩ ስፋት አንጻር እስከ አሁን በተቋሙ በተከናወኑ ሥራዎች የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

ስለሆነም መገናኛ ብዙኃን በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በሚፈጸሙ ስርቆቶች እየደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት የሚያሳዩ፣ የእኔነት ስሜትን የሚያሳድጉ እና የኃይል መሰረተ ልማቶችን ለመጠበቅ በወጡ ህጎችና አተገባበራቸው ላይ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የሚፈጥሩ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን በዕቅድ ይዘው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ስርቆቱ በኅብረተሰቡ ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ተቋሙ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሞገስ በኃይል መሠረተ ልማቱ ላይ የሚፈፀሙ ስርቆቶችን ለመከላከል ሚዲያዎች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሠጥተው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት ብቻ በስርቆት ምክንያት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ሲደርስበት የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን ደግሞ 200 ሚሊዮን ብር ለማውጣት መገደዱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top