ማመንጫ ጣቢያው ከዕቅድ በላይ ኃይል አምርቷል፤

ማመንጫ ጣቢያው ከዕቅድ በላይ ኃይል አምርቷል፤

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግልገል ጊቤ 2 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ2017 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከዕቅድ በላይ ኃይል ማምረቱን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ሹመት በላቸው እንደገለጹት ጣቢያው በሩብ ዓመቱ 565 ነጥብ 5 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማመንጨት አቅዶ 631 ነጥብ 53 ጌጋ ዋት ሰዓት በማምረት የዕቅዱን 111 ነጥብ 68 በመቶ ማሳካት ችሏል።

ጣቢያው በየወሩ በአማካይ እስከ 360 ነጥብ 59 ሜጋ ዋት ኃይል ሲያመርት እንደነበረም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

የጣቢያው አራቱም ተርባይኖች ውሃን ለመቆጣጠር የሚያገለግለው ሹል ጫፍ ያለው የብረት አካል ወይም ኖዝል በመበላቱ ምክንያት የአንድ ተርባይን የማመንጨት አቅም ከ105 ሜጋ ዋት ወደ 25 ሜጋ ዋት ድረስ ቀንሶ እንደነበር አቶ ሹመት አስታውሰዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ጉዳት የደረሰባቸውን የኖዝል አካላት በራስ አቅም በመጠገን አራቱም ዩኒቶች ወደ ሥራ መግባታቸው ለአፈጻጸሙ ከፍ ማለት በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

ከኖዝል በተጨማሪ የጣቢያውን ኃይል የማምረት አቅም አስተማማኝነት የሚያረጋግጡ የጥገና ሥራዎች ቀድመው መሰራታቸውም ለአፈጻጸሙ ከፍ ማለት ሚናቸው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ጣቢያው በበጀት ዓመቱ 1 ሺ 859 ነጥብ 13 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማምረት አቅድ እየሰራ ነው ያሉት አቶ ሹመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተመዘገበውን የተሻለ ውጤት አስጠብቆ በመቀጠል ዓመታዊ ዕቅዱን ለማሳካት የቅድመ መከላከል፤ የትንበያ እና የሁኔታ አመላካች ጥገና ሥራዎች በዕቅድ ተይዘው እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በ2002 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጊቤ 2 የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአራት ተርባይኖች 420 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አለው።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top