የሠራተኞችን ሙያዊ አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው

የሠራተኞችን ሙያዊ አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመልካ ዋከና የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሠራተኞችን ሙያዊ አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለፁ።

የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ በቀለ እንደተናገሩት የሠራተኞችን አቅም ለማጎልበት የሥራ ላይ ሥልጠና ከመስጠት ባለፈ ከመደወላቡ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ሠራተኞቹ ባሉበት ቦታ መምህራንን በማስመጣት በኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ምህንድስና የትምህርት መስክ ቅዳሜና እሁድ እያስተማረ ይገኛል፡፡

በዚህም በመጀመሪያው ዙር 21 ሠራተኞች የተመረቁ ሲሆን 17 የሚሆኑት ደግሞ በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡

የጣቢያው ኦፕሬሽን ሥራዎች ሳምንቱን ሙሉ 24 ሰዓት የሚከናወን በመሆኑ ትምህርት በሚኖር ጊዜ የተማሪዎች ሥራ በሌሎች ሠራተኞችና በጣቢያው ኃላፊዎች ጭምር እንደሚሸፈን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ሠራተኞች ከአሳሳ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመነጋገር እስከ ደረጃ 3 እንዲማሩ መድረጉን የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ አሁን ላይ ደግሞ ከበቆጂ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በደረጃ 4 ከሃምሳ በላይ የሠራተኛ ቤተሰቦችና የአካባቢው ወጣቶች እየተማሩ ናቸው ብለዋል።

ጣቢያው የመምህራንን ማረፊያ፣ የመመላለሻ ትራንስፖርት፣ የመማሪያ ክፍል እና በኃይል ማመንጫ ቤቱና በማከፋፊያ ጣቢያው ተግባር ተኮር ትምህርት የሚማሩበትን ሁኔታ ማመቻቸቱን ገልጸዋል።

ከትምህርትና ሥልጠና ተቋማቱ ጋር በመነጋገር በቀጣይ በሌሎች የትምህርት መስኮች እና በማስተርስ መርሀግብር ለማስተማር አቅዶ እየሰራ ነውም ብለዋል።

የሦስተኛ ዓመት የኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ምህንድስና ተማሪ የሆነው ፍቃዱ ጉዲሳ እንደገለጸው በደረጃ 3 ተመርቆ በጣቢያው ከስድስት ዓመት በላይ የቴክኒክ ባለሙያ ሆኖ ሠርቷል።

በጣቢያው የተመቻቸው የትምህርት ዕድል ሠራተኛው ሥራውን እየሰራ ሙያዊ አቅሙን የሚያሳድግበትና የእውቀት አድማሱን የሚያሰፋበት መሆኑን ገልጿል።

የጣቢያውን ሥራ በተሻለ ዕውቀት በማከናወን ውጤት ለማስመዝገብ አቅሙ የተገነባ ሠራተኛ መኖሩ አስፈላጊ ነው የሚለው ባለሙያው ለዚህም ጣቢያው ሠራተኛው የሥራ ስዓቱን ጭምር እየተሸፈነ እንዲማር በማድረጉ ምስጋናውን አቅርቧል።

ሌላኛዋ የጣቢያው ኦፕሬሽን ባለሙያና የ3ኛ ዓመት የኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ምህንድስና ተማሪ የሆነችው ካብታም ምንዳ በበኩሏ የትምህርት ዕድሉ ሴቶች ሙያዊ አቅማቸውን እንዲያሳድጉና የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ የሚረዳ መሆኑን ትናገራለች።

ቀደም ሲል አንዳንድ ወንድ ሠራተኞች ሩቅ ቦታ ሄደው ሲማሩ እንደነበረ ያወሳችው ባለሙያዋ የጣቢያው ሴት ሠራተኞች ግን ሥራቸውን ለቀው ካልሆነ በስተቀር ለመማር አስቸጋሪ እንደነበረ ተናግራለች።

አሁን ላይ ጣቢያው ባመቻቸው የትምህርት እድል ምክንያት ለመማር ሲል ሥራ ለቆ ለመሄድ ማሰቡን ትቶ ባለሙያው ተረጋግቶ ሳይጉላላ ትምህርቱን እየተማረ መሆኑን ገልጻለች።

የመዳወላቡ ዩኒቨርስቲ መምህርና የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ዲን የሆኑት ድንቁ ወርቁ ዩኒቨርስቲው የሚሰጠው ትምህርት ተማሪዎቹ በተግባር የሚያውቁትን ዘመኑ ከደረሰበት የእውቀት ደረጃ ጋር አዋህደው እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው ብለዋል።

መዳወላቡ ዩኒቨርስቲ የጣቢያውን ውጤታማነት ለማሳደግ በሚያስችሉ የሰው ሀብት ልማት ላይ ከጣቢያው ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የመልካ ዋከና የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 132 ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top