በለገጣፎ – ቃሊቲ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በደረሰ ጉዳት ምክንያት የወደቁ 5 የብረት ምሰሶዎችን በመጠገን ዳግም አገልግሎት መስጠት እስኪጀምሩ ድረስ የኃይል ፍሰት የማመጣጠን ሥራዎች እንደሚሰሩ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ አስታወቀ፡፡
በዘርፉ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ተወካይ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ግርማ ዘለቀ እንደገለፁት የብረት ምሰሶዎቹ የወደቁት በከባድ አውሎ ንፋስ ምክንያት ቢሆንም ቀደም ሲል በምሰሶዎቹ አካላት ላይ ይፈፀም የነበረው ተደጋጋሚ የስርቆት ወንጀል ለጉዳቱ መከሰት አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
በወደቁት የብረት ምሰሶዎች ላይ በተደረገው የቴክኒክ ፍተሻ መሰረት የተሰረቁ የምሰሶ አካላትን መልሶ ለመተካት በማሻሻያ (Modification) መልክ ይገጠሙ የነበሩት ብረቶች የምሰሶዎቹን መደበኛ ጥንካሬና የመሸከም አቅም ማምጣት አለመቻላቸው መረጋገጡን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የለገጣፎ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሙሉ በሙሉ ከአገልግሎት ውጪ እንዳልሆነና ከሱሉልታ በሚያገኘው አማራጭ የማስተላለፊያ መስመር አማካኝነት ኤሌክትሪክ እያቀረበ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ግርማ ገለፃ በአሁኑ ወቅት የብረት ምሰሶዎቹን መውደቅ ተከትሎ ወደ ሰሜን እና ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች በሚሄዱ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ያለውን የኃይል ፍሰት ለማመጣጠን ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
በዚህም የግሪድ ሥርዓቱን ደህንነት ለመጠበቅ እና የመስመሮችን መጨናነቅ ለማረጋጋት በደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ አቀስታ፣ ዓለም ከተማ፣ ወልዲያ፣ አላማጣ፣ መሆኒ፣ መቐለ፣ አዲግራት እና አድዋ እንዲሁም ሽሬ ከተሞች ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት በሚበዛበት (Peak hours) ወቅት እስከ 60 ሜጋ ዋት የሚጠጋ ኃይል እየተቀነሰ የኃይል ፍሰት የማመጣጠን ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከወደቁት ሦስት የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ውስጥ ለሁለት ምሰሶ የሚሆኑ ሙሉ አካላት ከተለያዩ አካባቢዎች መሰባሰባቸውን የገለፁት ተወካይ ሥራ አስፈፃሚው ቀሪዎቹ ደግሞ ከመቱ–ማሻ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ላይ ተለይተው መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።
ለአራት የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች አዲስ የመሰረት እና የዲዛይን ሥራ መጠናቀቁን ጠቅሰው በቀጣዮቹ ሳምንታት ውስጥ የሲቪል እና የምሰሶ ተከላ ሥራዎችን በማከናወን መስመሩ ዳግም በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
እንደ አቶ ግርማ ገለፃ በሌሎች የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይም መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱና የክትትል ሂደቱን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ዘርፉ የጥገና ሠራተኞች በሁሉም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ተገቢውን የፍተሻና ቁጥጥር ሥራዎች ለማከናወን ቦታው ድረስ መሄዳቸውን የሚያረጋግጥ በጂ.ፒ.ኤስ የታገዘ መተግበሪያ አልምቶ ለግምገማ ማቅረቡንና በቅርቡም ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በ230፣ 400 እና 500 ኪሎ ቮልት የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚስተዋለውን የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል ግዢ ለመፈጸም እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

