ከማብሪያና ማጥፊያ የሚዘለው የብርሃን ጉዞ

ከማብሪያና ማጥፊያ የሚዘለው የብርሃን ጉዞ

ብዙዎቻችን ቤታችን ስንገባ እንደምናገኘው የማብሪያና ማጥፊያ ቁልፍ ኃይልን የምናገኝበት እና ሲቋረጥም ወደነበረበት የምንመልስበት ሂደት ቀላልና አፍታ የማይወስድ ተግባር ይመስለናል። ነገር ግን ማብሪያና ማጥፊያውን በተጫንንበት ቅጽበት በቤታችን ወይም በሥራ ቦታችን የሚበራው የኤሌክትሪክ ኃይል እኛ ዘንድ ለመድረስ የሚያልፍበት መንገድ እጅግ ውስብስብ፣ አደገኛ እና በሺዎች የሚቆጠሩ የዘርፉ ባለሙያዎችን የሌሊትና ቀን የማይቋረጥ አድካሚ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ምን ያህል እንረዳለን፡፡

በሸለቆዎችና በበረሃዎች የሚጀመር የኃይል ማመንጨት ሂደት

የኃይል አቅርቦት ጉዞው የሚጀምረው ከኃይል ማመንጫዎች ነው። በኢትዮጵያ አብዛኞቹ የውሃ ኃይል ማመንጫዎች የሚገኙት ከመኖሪያ በራቁ አካባቢዎች፣ ከፍተኛ ንፋስና ሙቀት ባለባቸው በረሃዎች እና ሸለቆዎች ውስጥ ነው። በእነዚህ አስቸጋሪ አየር ጠባይና መልክዐ ምድር ውስጥ የሚሰሩ መሐንዲሶችና ቴክኒሻኖች ግዙፍ የውሃ እና የንፋስ ተርባይኖችንና ጄነሬተሮችን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ኃይል ያመነጫሉ። ከማመንጨት ሂደት በተጓዳኝ የሚከናወነው እያንዳንዱ የጥገናና የፍተሻ ሥራም ከፍተኛ አካላዊ ብርታትንና ሙያዊ ብቃትን የሚጠይቅ ነው።

በተራራ፣ በዱርና በገደል የተዘረጉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች

በሸለቆዎች እና በበረሃዎች የተመረተው ኃይል ወደ ከተሞችና ወደ እያንዳንዱ መኖሪያ ቤት ለመድረስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ አለበት። የኢትዮጵያ ወጣ ገባ መልክዐ ምድር ደግሞ ይህንን ጉዞ እጅግ አድካሚ ያደርገዋል። የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ግዙፍ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች (ታወሮች) የሚተከሉት፦

  • በከፍታኛ ተራራዎችና አደገኛ ገደሎች ላይ፣
  • ጥቅጥቅ ባሉ ዱሮች እና ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ ከመኖሪያ በራቁ ቦታዎች ላይ ነው።

እነዚህን መስመሮች መገንባት ብቻ ሳይሆን የተዘረጉትን መስመሮች በየጊዜው መፈተሽና መጠገን ሌላው ትልቅ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ሥራ ነው። መሐንዲሶች እና ቴክኒሻኖች በዝናብ፣ በሙቀት፣ በቁርና በንፋስ ሳይበገሩ መኪና በማይገባበት ቦታ ረጅም ርቀት በእግራቸው እየተጓዙ መስመሮቹን ይፈትሻሉ፤ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የጥገና ሥራዎችን ያከናውናሉ።

በማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚደረግ የሰከንድ ቁጥጥር

በኃይል ማመንጫዎች የተመረተውና በከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የተጓጓዘው ኃይል ወደ ከተሞች ሲደርስ በቀጥታ ወደ ተጠቃሚው ቤት አይገባም። በመጀመሪያ ወደ ማከፋፈያ ጣቢያዎች (Substations) ይገባል። እዚህ ቦታ የሚከናወነው ሥራ ደግሞ የሰከንዶች መዘናጋትን አይፈቅድም።

  • የኃይል አቅርቦት ስርዓቱ ቮልቴጅ እንዳይዋዥቅ፣ መሣሪያዎች እንዳይቃጠሉና አጠቃላይ የኃይል ቋት (Grid) እንዳይረበሽ ለማድረግ በ24 ሰዓት ውስጥ ለደቂቃ እንኳ ያልተቋረጠ ክትትል ይደረጋል።
  • ማንኛውም ተፈጥሮአዊ ወይም ቴክኒካዊ ችግር ሲከሰት ወዲያውኑ አስተካክሎ የኃይል መቋረጥን ለመከላከል ኢንጂነሮች ሌሊትና ቀን በንቃት ይሰራሉ።

ስለሆነም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት  የማብሪያ ማጥፊያ ቁልፍ በመጫን የሚወሰን ቀላል አሰራር አይደለም። ከእያንዳንዱ የበራ አምፖል ጀርባ በበረሃ ሙቀትና ወበቅ እንዲሁም በገደላማ ቦታዎች የሚደረግ አድካሚ ፍተሻ፣ በከፍተኛ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚደረግ ያልተቋረጠ የቮልቴጅ ክትትል እና የብዙ ሰዎች እረፍት አልባ ድካም አለበት። ይህን ውስብስብ ሂደትና የመሰረተ ልማቱን ደህንነት ለኃይል አቅርቦቱ የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ በመገንዘብ ኃይልን በአግባቡ መጠቀም የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

Scroll to Top