ብዙ ጊዜ የኤልኒኖ ክስተት ሲነሳ አእምሯችን ወደ ድርቅ፣ የምግብ እጥረት እና የግብርና መስተጓጎል ያደላል። ነገር ግን ኤልኒኖ ከአየር ጠባይ መዛባት ባሻገር በቀጥታ ከምንጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና ደህንነት ጋር እጅግ ጥብቅ የሆነ ትስስር አለው።
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አብዛኛው የኤሌክትሪክ ኃይላቸውን ከውሃ (Hydropower) በሚያመነጩ ሀገራት ላይ የኤልኒኖ መከሰት በኃይል አቅርቦት ስርዓቱ ላይ ግዙፍ ፈተና ይደቅናል።
1. የኤልኒኖ ክስተት ምንድን ነው?
ኤልኒኖ በፓሲፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚከሰት የአየር ጠባይ መዛባት ሲሆን የውቅያኖሱ ወለል የሙቀት መጠን ከተለመደው በላይ ሲጨምር የሚከሰት ነው። ይህ የሙቀት መጨመር፡-
- የዓለም አቀፍ የንፋስና የዝናብ ስርጭትን ያዛባል።
- ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ የክረምት ዝናብ ስርጭትን በመቀነስ ለከፍተኛ ድርቅ እና የውሃ እጥረት ይዳርጋል።
- በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ያልተለመደ ከባድ ጎርፍ ያስከትላል።
2. የኤልኒኖ ክስተት እና የኃይል አቅርቦት ትስስር
የኤልኒኖ ክስተት በኃይል አቅርቦት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
ሀ. የውሃ ግድቦች ይዞታ መቀነስ
በኢትዮጵያ ከ90% በላይ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመረተው ከውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ነው። ኤልኒኖ በሚከሰትበት ወቅት የክረምት ዝናብ ስርጭት ስለሚቀንስ ወደ ግድቦች የሚገባው የውሃ መጠን ሊቀንስ ይችላል። በግድቦች ውስጥ ያለው የውሃ መጠን ከዝቅተኛው የማመንጫ ከፍታ በታች ሲወርድ ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ኃይል ማመንጨት እንዳይችሉ ሊያደርግ ይችላል።
ለ. የኃይል እጥረት እና ፈራረቃ (Rolling Blackouts / Load Shedding)
በኤልኒኖ ምክንያት የሚፈጠረው የውሃ እጥረት የኤሌክትሪክ አቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል፡፡ የኃይል አቅርቦት ስርዓቱ እንዳይዛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከላት ኃይል በፈረቃ ለማድረስ እንዲገደዱ ምክንያት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ በኢንዱስትሪዎች፣ በንግድ ተቋማት እና በመኖሪያ ቤቶች ላይ የኃይል መቋረጥን ያመጣል።
ሐ. የኤሌክትሪክ ፍላጎት መጨመር (Demand Surge)
ኤልኒኖ ድርቅን ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሙቀት መጨመርን ይዞ ይመጣል። በሞቃት አየር ምክንያት ሰዎች ማቀዝቀዣዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጠቀሙ በኃይል አቅርቦት ሥርዓቱ ላይ ጫና ይፈጥራል።
መ. አማራጭ የኃይል ምንጮች ውድነት እና የካርቦን ልቀት
የውሃ ኃይል ማመንጨት በሚቀንስበት ጊዜ ሀገራት የኃይል ክፍተቱን ለመሙላት በነዳጅ ወይም በከሰል ድንጋይ ወደሚሰሩ የሙቀት ኃይል ማመንጫዎች (Thermal Power Plants) ያደላሉ። ይህ ደግሞ ለነዳጅ ግዥ የሚወጣውን የውጭ ሀገር ገንዘብ (Foreign Currency) ያንራል፤ የአካባቢ ብክለትን እና የካርቦን ልቀትን ያባብሳል።
የኤልኒኖን ተፅዕኖ ለመቋቋም መወሰድ ያለባቸው ስልታዊ መፍትሔዎች
የኤልኒኖን አደጋ አስቀድሞ በመገንዘብ የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግ
- የኃይል ምንጮችን ማሰባጠር
- የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት
- ዘመናዊ የትንበያ ዘዴዎችን መጠቀም እና
- የኃይል ቁጠባ ላይ ትኩረት ማድረግ ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው፡፡