በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአካባቢ ጥበቃ እና የደን ሽፋን ማሳደጊያ ስልት ብቻ አይደለም። ከዚህ ባሻገር የሀገሪቱን የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ለሆኑት የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ህልውና እና ዘላቂነት እጅግ ወሳኝ የሆነ ግብዓት ነው።
ከ90% በላይ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ከውሃ የምታመነጨው ኢትዮጵያ የግድቦቿን ህልውና ለማስጠበቅ እና አቅማቸውን ለማጎልበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከግድቦች ደህንነት እና ጥበቃ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው። የአረንጓዴ አሻራ ከአባባቢ ጥበቃ በዘለለ በርካታ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡
1. የደለል ክምችትን የመከላከል ሚና
የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በአግባቡ ኃይል እንዳያመነጩ ከሚያደርጓቸው ችግሮች መካከል አንዱ የደለል ክምችት ነው። የደን ጭፍጨፋ እና የአፈር መሸርሸር በሚኖርበት ጊዜ ከባድ የክረምት ዝናብ ለም አፈርን እያጠበ ወደ ወንዞች እና በቀጥታ ወደ ግድቦች እንዲገባ ያደርጋል፡፡
ደለል በግድቦች ውስጥ ሲከማች የግድቦቹን ውሃ የመያዝ አቅም (Reservoir Capacity) በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። በተጨማሪም ደለል የተቀላቀለበት ውሃ ወደ ተርባይኖች ሲገባ ተርባይኖቹን እና ሌሎች መሳሪያዎችን የአገልግሎት ጊዜ ሊያሳጥር ይችላል።
ስለሆነም አረንጓዴ አሻራ ለእንደዚህ ዓይነት ችግር ሁነኛ መፍትሔ ነው፡፡ በተፋሰሶች እና በወንዞች መነሻ አካባቢዎች የሚተከሉ ዛፎች እና የዕፅዋት ሽፋኖች የአፈር መሸርሸርን ይከላከላሉ። የዛፎች ሥሮች አፈርን አጥብቀው በመያዝ ውሃው ብቻ ወደ ግድቡ እንዲገባ ያደርጋሉ፤ ይህም የግድቦችን የአገልግሎት ዘመን ያራዝማል።
2. የከርሰ ምድር ውሃን ማጎልበት
ዛፎች ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ውሃው በቀጥታ መሬት ላይ እንዳያርፍና አፈር በውሃ ታጥቦ እንዳይሄድ ይከላከላሉ፡፡ ሥራቸውን ውሃ ወደ መሬት ውስጥ እንዲሰርግ ያደርጋል። መሬት ውስጥ የሰረገው ውሃ ደግሞ በበጋ ወቅትና በድርቅ ጊዜ በምንጮች አማካይነት ቀስ እያለ ወደ ዋና ዋና ወንዞች ይፈስሳል።
ይህ ሂደት በበጋ ወቅት የወንዞች የውሃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይቀንስ በማድረግ ግድቦች ዓመቱን ሙሉ ያልተቋረጠ ኃይል እንዲያመነጩ ያግዛቸዋል።
3. የአየር ንብረት መዛባትንና ድርቅን የመቋቋም አቅም
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የአየር ንብረት መዛባቶች (እንደ ኤልኒኖ ያሉ) የዝናብ ስርጭትን ያዛባሉ። ሰፊ የደን ሽፋን ያለበት አካባቢ የአየር ጠባዩ ከመስተካከሉም በላይ የዝናብ ስርጭቱ እንዲስተካከል አስተዋጽኦ ያደርጋል።
አረንጓዴ አሻራ በሀገር አቀፍ ደረጃ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ከማገዙም በላይ በድርቅ ወቅት የሚከሰተውን ከፍተኛ የውሃ ትነት በመቀነስ በግድቦች ውስጥ ያለው ውሃ በሙቀት ምክንያት እንዳይደርቅ ይከላከላል።
4. የኢኮኖሚ እና የመሰረተ ልማት ደህንነት
አንድ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለመገንባት ቢሊዮን ዶላሮች ይወጣሉ። በኃይል ማመንጫ ግድቦቹ ውስጥ ደለል የሚከማች ከሆነ ደግሞ የግድቦቹ የማመንጨት አቅም ሊቀንስ ወይም ለጥገና የሚወጣው ወጪ እንዲንር ያደርጋል።
በአጠቃላይ አረንጓዴ አሻራ እና የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቦቻችን የነፍስና የስጋ ያህል የተሳሰሩ ናቸው። ግድቦችን መገንባት የኃይል መሰረተ ልማት መዘርጋት ሲሆን በአረንጓዴ አሻራ ዛፎችን መትከል ደግሞ ያንን መሰረተ ልማት ህያው አድርጎ የመጠበቂያ የተፈጥሮ ጋሻ ነው።
ስለሆነም እያንዳንዱ የምንተክለው ችግኝ አፈርን ከመሸርሸር የሚከላከል፣ የግድቦቻችንን ዕድሜ የሚያራዝም እና ለቀጣዩ ትውልድ የማያቋርጥ የብርሃንና የኃይል ምንጭ የሚያረጋግጥ ሀገራዊ አሻራ ነው።