የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሠራተኞች ለሲሞን ፔትሮ ሳሊኒ የመታሰቢያ ፕሮግራም አካሄዱ

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሠራተኞች ለሲሞን ፔትሮ ሳሊኒ የመታሰቢያ ፕሮግራም አካሄዱ

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሠራተኞች ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የቀድሞ ሳሊኒ ኩባንያ የአሁኑ ዊ ቢውልድ ግሩፕ መስራች እና ባለቤት ለነበሩት ለሲሞን ፔትሮ ሳሊኒ የመታሰቢያ ፕሮግራም አካሂደዋል።

በዊ ቢውልድ ኩባንያ የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር  ስቲፋኖ ሲልቪ በፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት በሲሞን ፔትሮ ሳሊኒ አመራር ሰጭነት ኩባንያው በኢትዮጵያ በርካታ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ለአገልግሎት አብቅቷል።

ኩባንያው በኢትዮጵያ በለገዳዲ የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ላይ ሥራ እንደጀመረም ጠቁመዋል።

ኩባንያው በኃይል መሠረተ ልማት ዘርፉም የጊቤ 1፣2፣ 3 እና ጣና በለስ ማመንጫ ጣቢያዎችን በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃት የቻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ኮይሻ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ይገኛል።

ሲሞን ፔትሮ ያከናወኑት ሥራ እና አሻራቸው በሁሉም አዕምሮ  ሲታወስ የሚኖር ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ  ሌጋሲያቸውን ለማስቀጠል የኩባንያው ሠራተኞች በቡድን ስሜት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ሥራ አስኪያጁ በሲሞን ፔትሮ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘን ገልፀው ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የዊቢውልድ ግሩፕ እና ለፕሮጀክቱ ሠራተኞች መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮይሻ ማመንጫ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አባይነህ ጌትነት በበኩላቸው ኩባንያው በኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን በጥራት በመገንባት ለኃይል ልማት ዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

ኩባንያው ከፕሮጀክቶች የግንባታ ሥራ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም የሠለጠነና ልምድ ያለው ባለሙያ በማፍራት ለእውቀትና ቴክኖሎጅ ሽግግር የራሱን አስተዋፅዖ  እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ዊ ቢውልድ በኢትዮጵያ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንዳለውና የሌሎች ኩባንያዎች አመራሮችም በአቋራጭ ሳይሆን በረጅም ጊዜ ዕቅድ ውጤታማ እንደሚሆኑ ከሳሊኒ ትምህርት ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።

የ10 ልጆች አባት የነበሩት ሲሞን ፔትሮ ሳሊኒ በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም እንደተለዩ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top