ተቋሙ ለሰብዓዊ ድጋፍ ላበረከተው አስተዋፅኦ ዕውቅና ተሰጠው

ተቋሙ ለሰብዓዊ ድጋፍ ላበረከተው አስተዋፅኦ ዕውቅና ተሰጠው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ እያከናወነ ላለው ሥራ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶለታል።

ሽልማቱን ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ እና ከክልሉ የቀይ መስቀል ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ እና አቶ ንጋቱ ዳንሳ የተረከቡት በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር እና የሰብዓዊ እርዳታውን ለመከታተል የተዋቀረው ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ መኮንን ናቸው፡፡

ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት ተቋሙ በደንብ ከተሰጠው ኃይል የማመንጨት ተልዕኮ ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሰብዓዊ ድጋፎች ላይ በትኩረት እየተሳተፈ ይገኛል።

ባለፈው ዓመት በደቡብ ኦሞ ዞን ለሚገኙ በዝናብ እጥረት ለድርቅ ለተጋለጡ አራት ወረዳዎች የተደረገውን የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ድጋፍንም ለአብነት አንስተዋል።

ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የተበረከተው እውቅና በቀጣይ ተቋሙ በሰብዓዊ ድጋፎች ላይ በተሻለ መልኩ እንዲሰራ መልዕክት የሚያስተላልፍ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት የአስተዳደራዊ ጉዳዮችና ዶኩመንቴሽን ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ በበኩላቸው ተቋሙ ለማህበራዊ ኃላፊነት ትኩረት በመስጠት በተቋም ደረጃ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አባል ሆኗል።

ተቋሙ በየዓመቱ ከሚከፍለው የአባልነት መዋጮ በተጨማሪ ሠራተኞቹ የማህበሩ አባል እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሰብዓዊ እርዳታውን ለመከታተል የተዋቀረው ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው ተቋሙ ማህበራዊና አካባቢያዊ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ ፕሮጀክቶቹ ባሉባቸው አካባቢ የተደራጀ ጥናት በማድረግ እና ምላሽ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ተቋሙ ለተሰጠው ዕውቅና በተቋሙ የተቋቋመው የሰብዓዊ ድጋፍ ኮሚቴ አባላት ሚና የጎላ እንደነበር ተገልጿል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top