በደቡብ ኦሞ ዞን ለተደረገው የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ የማጠቃለያ መርሀ ግብር ተካሄደ

በደቡብ ኦሞ ዞን ለተደረገው የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ የማጠቃለያ መርሀ ግብር ተካሄደ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በደቡብ ኦሞ ዞን በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ አጋጥሞ ለነበረው የምግብ እጥረት ያደረገው የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ድጋፍ የማጠቃለያ መርሀ ግብር ተካሄደ።

በዞኑ ሐመር፣ ዳሰነች፣ ኛንጋቶም እና ሳላማጎ ወረዳዎች የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ስርጭቱን ለመገምገም ያለመ  የማጠቃለያ ፕሮግራም በዛሬው ዕለት በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ተወካይና የክልሉ ቀይ መስቀል ማህበር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቦርድ አባል አቶ ንጋቱ ዳንሳ መርሀ ግብሩን ሲከፍቱ እንደተናገሩት በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት በሚከሠቱ ሠው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ፈላጊ እየሆኑ ይገኛሉ።

ባለፉት ዓመታት በደቡብ ኦሞ ዞን አራት ወረዳዎች ላይ ባጋጠመው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያትም በርካታ ዜጎች ለምግብ እጥረት ተጋልጠው እንደነበር አቶ ንጋቱ አስታውሰዋል።

ያጋጠመውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ  ክልሉ ባቀረበው የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ጥሪ መሠረት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 260 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ማድረጉን አቶ ንጋቱ ተናግረዋል። ተቋሙ የክልሉን ጥሪ  ተቀብሎ ላደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንደተሰራጨና ከዚህም በርካታ ልምዶች እንደተገኙበት አቶ ንጋቱ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአካባቢው የሚስተዋለውን የተፈጥሮ አደጋ ለመቀነስና በዘላቂነት ለመፍታትም ሁሉም በትብብር መስራት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

ተቋሙ የማህበራዊ ድጋፎች ላይ እንዳደረገው ሁሉ በክልሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት  የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ታዓ በበኩላቸው ማህበሩ በሀገሪቱ በሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮች በህብረተሰቡ ላይ የሚደርሱ ስቃዮችን ለማቃለል ጥረት እያደረገ ይገኛል።

በተጠናቀቀው ዓመትም ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ ለ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ድጋፎች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን በአራቱ ወረዳዎች  ለተከሰተው የምግብ እጥረት በሁለት ዙር ለ191 ሺ 395 ዜጎች የተለያዩ ድጋፎችን ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ አንስተው ተቋሙ ማህበረሰቡ ድጋፍ በሚፈልግበት ጊዜ በመድረስ ላደረገው ወቅታዊ ምላሽ  አመስግነዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደተናገሩት ተቋሙ ከኃይል መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ጎን ለጎን በጥናት ላይ በመመስረት የተለያዩ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በደቡብ ኦሞ ዞን የተደረገውን ድጋፍ የስርጭት ሥራ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር  ልምዱን ተጠቅሞ  እንዲያከናውን መደረጉን አስታውሰው ተቋሙም ሂደቱን በመከታተል እርዳታው በፍትሃዊነት ተደራሽ መደረጉን ማረጋገጥ ችሏል ብለዋል።

ተቋሙ ካደረገው ጊዜያዊ ድጋፍ ባለፈ  በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

ከማህበራዊ ድጋፍ ሥራዎች በተጨማሪ በአካባቢው የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ መጀመሩን ጠቁመው ሁሉም ህብረተሰብ በአካባቢው ለሚገኙ የኃይል መሠረተ ልማቶች ጥበቃ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ባጋጠመው የመሬት መንሸራተት ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ዳይሬክተሩ በተቋሙ ስም ሀዘናቸውን ገልፀዋል።

ተቋሙ ካደረገው 259 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ውስጥ 258 ነጥብ 56 ሚሊዮኑ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 213 ነጥብ 27 ሚሊዮን ብሩ ለምግብና ምግብ ነክ፣ 28 ሚሊዮን ብሩ ለእቃ ማጓጓዝ እንዲሁም ቀሪው 18 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብሩ ደግሞ ለሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎች የዋለ መሆኑን በአውደ ጥናቱ ላይ ተመልክቷል።

የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አቶ ኩያ ሉኩ ተለምየ እና አቶ ሉቡኮ ላሌ ተቋሙ ባደረገው ድጋፍ ህይወታቸውን መታደግ እንደቻሉና በቀጣይ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል።

በማጠቃለያ አውደ ጥናቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ የኃላፊዎችን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቀይ መስቀል ማህበርና አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የወረዳዎቹ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ድጋፍ የተደረገላቸው የማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በዕለቱም በክልሉ ጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቻ ሻቻ ጎዝዴ ቀበሌ ባጋጠመው የመሬት ናዳ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የህሊና ፀሎት ተደርጓል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top