የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮንትራት በመውሰድ በአዲስ አበባ ከተማ ዓለም ባንክ አካባቢ አዲስ የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ መጀመሩን በተቋሙ የራስ ኃይል ግንባታ መምሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የፕሮጀክት ማኔጅመንት II ሥራ አስኪያጅ አቶ ተድላ ሰይፉ እንደገለፁት የግንባታ ስምምነቱ 33 ኪ.ቮ አቅም ያለውን የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ገንብቶ ማስረከብ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ወጪ እየተገነባ የሚገኘው ፕሮጀክቱ 31 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት የተያዘለት መሆኑን አቶ ተድላ ተናግረዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ሥራ የሲቪል፤ የኤሌክትሮ ሜካኒካል እንዲሁም የፍተሻ እና የሙከራ ሥራዎችን እንደሚያካትትም ነው የገለፁት፡፡
እንደ አቶ ተድላ ገለፃ ተቋሙ አሁን የጀመራቸው ግንባታዎች ላለፉት በርካታ ዓመታት ለውጭ ሀገር የሥራ ተቋራጮች ይሰጡ ነበር፡፡
ይሁንና ከግንባታ እስከ ፍተሻ ያለው ሥራ በሀገር ውስጥ አቅም በመሰራቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረቱም ባሻገር ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስችል መደላድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡
የፕሮጅክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዮሐንስ መልካሙ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ግንባታ ግንቦት 2016 ዓ.ም መጀመሩን እና በስድስት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ኢንጂነር ዮሐንስ ገለፃ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ከ41 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን የመቆጣጠሪያ ክፍል፣የስዊች ጊር ስትራክቸር፣ የትራንስፎርመር ማስቀመጫ ግንባታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
ለኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች የሚያስፈልጉ ግብአቶችን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚያቀርብ የገለፁት የፕሮጀክቱ የሳይት መሀንዲስ አቶ ሶፎኒያስ ካሱ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ለ55 የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው ስምንት ወጪ መስመሮች ሲኖሩት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የኃይል ጫና ከማቃለሉም ባሻገር ከጣቢያው 50 ኪ.ሜ ዙሪያ ለሚገኙ ፋብሪካዎች እና ከተሞች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ያስችላል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”







