በኮይሻ ጉብኝት ያደረጉት የፌደራል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አሻራቸውን አኖሩ

በኮይሻ ጉብኝት ያደረጉት የፌደራል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አሻራቸውን አኖሩ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና የተለያዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አከናውነዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉና ተጨማሪ ውሃ እንዲይዙ እያገዘ ይገኛል።

የተቋሙ ሠራተኞች በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ተቋሙ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን እየተከለ  እንደሆነ ገልፀዋል። 

ሠራተኛው በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ላይ በስፋት መሳተፍ እንደሚኖርበት አሳስበዋል።

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ መብራቱ ተሾመ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የአካባቢውን ሥነ ምህዳር በመጠበቅ የሥራ ቦታዎችን ለኑሮ ምቹ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የአዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ባልቻ እና በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው በኩረፂዮን በኮይሻ ፕሮጀክት አካባቢ የአረንጓዴ አሻራቸውን በማሳረፋቸው እንደተደሰቱ ገልፀዋል።

መርሃ ግብሩ የአካባቢን ገፅታ ለመቀየርና አረንጓዴ  አካባቢን ለትውልድ ለማስተላለፍ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

በፕሮጀክቱ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ደሳለኝ እና በዩ ቢዩልድ ኩባንያ የኢንቫይሮሜንታል መሃንዲስና የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ አስተባባሪ ሄኖክ ቼኮል እንደተናገሩት በፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ምክንያት የተጎዱ ቦታዎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ሲባል የችግኝ ተከላ ሥራው በሀገር አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከመከናወኑ በፊት መጀመሩን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ ሠራተኛ የችግኝ ተከላ ሥራውን እንደ ዋና ሥራ በመያዝ መኖሪያ ቦታውን ምቹ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ የተተከሉት ችግኞች አሁን ላይ ፍሬ ማፍራት መጀመራቸውን እና ሠራተኛውም ለምግብነት እየተጠቀመበት እንደሚገኝ ተገልጿል።

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “የምትተክል ሃገር፣ የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ ይገኛል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top