የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራሮችና ሠራተኞች የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ባለሥልጣን ተጠሪ የሆኑ ተቋማት ከኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው ሞጆ ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ላይ ችግኝ ተክለዋል።
የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “የምትተክል ሀገር፣ የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ይገኛል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ደዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል እንደገለጹት የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራሙ ጽዱና አረንጓዴ አካባቢን በመፍጠር የምግብ ዋስትናዋን ያረጋገጠች ጀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ሚና አለው።
በመሆኑም የመንግስት ልማት ድርጅቶች ከተጠሪ ተቋማት ጋር የሚያካሂዱት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ጋር ተሳስሮ እየተፈጸመ ይገኛል ብለዋል።
ከአሁን ቀደም የተተከሉ ችግኞች በጀት ተመድቦ ክትትልና ቁጥጥር በመደረጉ ከ90 በመቶ በላይ መጽደቃቸውን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞችም እንዲጸድቁ ተጠሪ ተቋማቱ በኃላፊነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንደገለጹት ተቋሙ ከተጣለበት አገራዊ ኃላፊነት ባሻገር ባለፉት ዓመታት በተከናውኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሮች ላይ በንቃት ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡
ተቋሙ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ባለሥልጣን ተጠሪ የሆኑ ተቋማት በሚያከናውኑት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ከመሳተፍ በተጨማሪ በሁሉም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የተጠናከረ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም እያካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአካባቢ ጥበቃን ለማጎልበት ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የተቀዳ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት እና በማስተላለፍ አረንጓዴ እና ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ተቋሙ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ለአራተኛ ጊዜ እየተሳተፉ መሆናቸውን የገለጹት አቶ መርክነህ ይገዙ በተቋሙ የሕግ መምሪያ ዳይሬክተር ሁሉም ሠራተኛ ለአገራዊ መርኃ ግብሩ ስኬት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በየዓመቱ የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከደለልና ጎርፍ በመከላከል እንዲሁም ተፈጥሯዊ የዝናብ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላኛዋ ተሳታፊ በተቋሙ የሠራተኛ አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ምዕራብ ጋሹ በበኩላቸው ለ3ኛ ጊዜ እየተሳተፉ መሆኑንና በዚህም መደሰታቸውን ተናግረዋል።
መትከል ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ለውጤት እንዲበቁ በማድረግ በኩል ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በችግኝ ተከላ መርሃግብሩ ላይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል፣ የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ኃላፊ አቶ ሙሱጠፋ አባሲመል፣ የሞጆ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባን ጨምሮ አስራ ሁለት የመንግሥት የልማት ድርጅት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳትፈዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”








