የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብሩ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው

የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብሩ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራሮችና ሠራተኞች “የምትተክል ሀገር፣ የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር አካል የሆነ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በሞጆ ሀዋሳ ፈጣን መንገድ ላይ አከናውነዋል።

በተቋሙ የኢንጅነሪንግ ሥራ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ወድነህ የማነ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫዎችን ከመገንባትና ከማስተዳደር ባለፈ በአረንጓዴ አሻራው ሀገራዊ መርሀ ግብር ላይ በመሳተፍ ጉልህ አሻራውን እያኖረ ይገኛል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከደለል ለመከላከል እንዲሁም በቂ ውሃ እንዲያገኙ በማድረግ የግድቦችን ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም ተቋሙ ለሀገር ዕድገትና ለአህጉራዊ የኃይል ትስስር መሰረት የሚሆን አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያግዘው ኢንጂነር ውድነህ ጠቁመዋል።

ተቋሙ ለሚተገብራቸው ሀገራዊ ስትራቴጅዎች የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ ሚናው የጎላ ነው ያሉት ኢንጂነር ውድነህ ፕሮግራሙ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበር ሠራተኛውና አመራሩ ድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

በተቋሙ የማከፋፈያ ጣቢያዎችና ማስተላለፊያ መስመሮች ግንባታ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ክብሮም ካህሳይ በበኩላቸው ተቋሙ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሮች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ ተቋሙ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት እና በማስተላለፍ አረንጓዴ እና ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እየሰራ ላለው ሥራ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች በሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ላይሁሉም ሰው በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ የሚገኙ የተቋሙ ሠራተኞች ችግኞቹን ከመትከል ባለፈ በመንከባከብና በመከታተል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአረንጓዴ አሻራ በተሰጠው ትኩረት አሁን ላይ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን መሰረት ባደረገ የደን ሽፋን ልኬት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top