የኮንዳክተር ቅየራው 83 በመቶ ተጠናቋል

የኮንዳክተር ቅየራው 83 በመቶ ተጠናቋል

ከሁርሶ – ድሬዳዋ ቁጥር 3  ማከፋፈያ ጣቢያ የተዘረጋውን ባለ 132 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር የመቀየር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ አስታወቀ።

በዘርፉ የማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና ማስተባበሪያ ቢሮ ቁጥር ሁለት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀሐይነህ አበበ እንደገለጹት የኮንዳክተር ቅየራው  23 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን እና በ84 የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የሚከናወን ነው። 

መስመሩ ከ28 ዓመት በላይ ያገለገለና የኮንዳክተሩ ዓይነትና መጠን አሁን ካሉት የኮንዳክተር ገመዶች ያነሰ በመሆኑ ለኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት እንደነበር ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል።

የቅየራ ሥራው በዓይነትና በመጠን ከፍ ያለ አቅም ያለው እና የኃይል ጭነትን መሸከም የሚችል ኮንዳክተር በመተካት በአካባቢው አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የኮንዳክተር ቅየራው ሲጠናቀቅ የኃይል መቆራረጥን ከማስቀረቱ በተጨማሪ በሌሎች መስመሮች ላይ እክል ቢያጋጥም በአካባቢው ኃይል እንዳይቋረጥ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

አሁን ላይ ኮንዳክተሩን የመቀየር ሥራው በ70 ታወሮች ላይ የተከናወነ ሲሆን አጠቃላይ አፈጻጸሙም 83 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ በቀሪ 14 ታወሮች ላይ የቅየራ ሥራውን  በአጭር ቀናት በማጠናቀቅ መስመሩን አገልግሎት ለማስጀመር በትጋት እየተሠራ ነው።

ሥራው የሚከናወነው በራስ አቅም መሆኑ  የዕውቀት ሽግግር ከማድረጉ በተጨማሪ የፕሮጀክት አስተዳደር አፈጻጸምን በማሻሻል ሥራዎችን በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት ለማከናወን ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top