ኃይል ሳይቋረጥ የኮንዳክተር ቅየራ ሥራ እየተከናወነ ነው

ኃይል ሳይቋረጥ የኮንዳክተር ቅየራ ሥራ እየተከናወነ ነው

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ጉዳት የደረሰበትን የለገጣፎ- ኮምቦልቻ- አላማጣ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ ሁለተኛ ሰርኪዩት መስመር ኃይል ሳይቋረጥ በአዲስ ኮንዳክተር የመቀየር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የራስ ኃይል መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የለገጣፎ- ኮምቦልቻ- አላማጣ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ሁለተኛ ሰርኪዩት ሆት ላይን የኮንዳክተር ዝርጋታ ፕሮጀክት የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ነጋ እንዳስታወቁት ኮንዳክተሩን የመቀየር ሥራው ከ86 ነጥብ 8 በመቶ በላይ ተከናውኗል።

የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታው ከ2013 ዓ.ም በፊት ተጠናቆ ለፍተሻና ሙከራ ሥራ ዝግጁ እንደነበር ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ በወቅቱ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት መስመሩ መጎዳቱን ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ዮሐንስ ገለፃ ፕሮጀክቱ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን መስመሮች በመለየትና በአዲስ ኮንዳክተር በመቀየር ለህብረተሰቡ ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ እየሰራ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ ዮሐንስ የመጀመሪያው ምዕራፍ ከለገጣፎ- ኮምቦልቻ 61 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ሁለተኛው ምዕራፍ ከኮምቦልቻ- አላማጣ 114 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ የለገጣፎ- ኮምቦልቻ የኃይል ማሰተላለፊያ መስመር የኮንዳክተር ቅየራ ሥራ መጠናቀቁን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ይህም ከመስመሩ ኃይል ለሚያገኙ አካባቢዎችና ለለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ አስተማማኝ እሌክትሪክ ለማቅረብ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሁለተኛው ምዕራፍ የኮምቦልቻ- አላማጣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የኮንዳክተር ቅየራ ሥራ የአንደኛው ሰርኪዩት መስመር ኃይል ሳይቋረጥ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው የገለፁት፡፡

ይህም በኮምቦልቻና አጎራባች ከተሞች በኤሌክትሪክ መቋረጥ ሳቢያ ሊፈጠር የሚችለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማስቀረት የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል፡፡

የመስመር ዝርጋታውን ኃይል ሳይቋረጥ ማከናወን መቻሉ ለተቋሙ ትልቅ እምርታ መሆኑን ያብራሩት አቶ ዮሐንስ ሥራው በተቋሙ የራስ ኃይል መምሪያ ሠራተኞች አቅም እንዲከናወን መወሰኑ የዕውቀትና ልምድ ሽግግር እንዲኖር በር የከፈተ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

የለገጣፎ- ኮምቦልቻ- አላማጣ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ሁለተኛ ሰርኪዩት ሆት ላይን የኮንዳክተር ዝርጋታ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ ከ86 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተያዘ ሲሆን የፋይናንስ ወጪውም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸፈም ነው፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top