በቆቃ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ መጪውን የክረምት ወራት ታሳቢ ያደረገ የግድብ ደህንነት ክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጣቢያው የጥገና ክፍል ኃላፊ አስታወቁ።
ኃላፊው አቶ ያፌት ተስፋዬ እንዳስታወቁት በክረምት ወራት ሊኖር የሚችለው ዝናብ ለኃይል ማመንጫዎች አስፈላጊ ቢሆንም በግድቦች ላይ ተገቢው የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ ካልተከናወነ ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል ።
በክረምት ወራት በእድሜ ምክንያት እያጋጠሙ ያሉ ስንጥቆች እንዲሁም የእንቦጭ አረምና ደለል በግድቡ ደህንነትና ኦፕሬሽን ሥራ ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድሩ ጠቁመዋል።
በመሆኑም መጪውን የክረምት ወራት ታሳቢ በማድረግ እነዚህን ችግሮች ለመከላከል አጠቃላይ የግድብ ፍተሻ እና የቅድመ መከላከል የጥገና እንዲሁም የክትትል ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የክትትልና ቁጥጥር ሥራው በውኃ መግቢያው፣ በውኃ ማስተንፈሻ (Spillways) እና በግድቡ የተለያዩ ክፍሎች ላይ እንደሚከናወን ገልፀዋል።
በዚህም የግድቡን የውኃ ማስተንፈሻ እና መቆጣጠሪያ በሮች በመጠገንና ብረቶቹን ከዝገት በመከላከል ለሥራ ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በግድቡ የላይኛው ክፍል ላይ የሚገኙ ስንጥቆች እየሰፉ እንዳይሄዱ ክፍተቶቹን የሙሙላት ሥራ መከናወኑንም አብራርተዋል።
እንደ አቶ ያፌት ገለፃ የግድብ ደህንነት ሥራው በክረምት ወራት ወደ ግድቡ የሚገባውን ክፍተኛ ውኃ ለማስተንፈስ በሮቹ በትክክል አንደሚከፈቱ፣ እንደሚዘጉ እና ብሬከሩ በትክክል እንደሚስራ አስቀድሞ ለመለየት ይጠቅማል።
የቅድመ ፍተሻና እና ጥገና ሥራው ግድቡ ውኃ ከሞላ በኋላ የተበላሹ በሮች፣ ሞተሮች፣ ብሬከሮች እና የተለያዩ መሣሪያዎችን ለመጠገን የሚፈጥረውን የሥራ ጫና እንደሚያቀል አብራርተዋል።
የክትትልና ቁጥጥር ሥራው የግድቡን ደህንነት በመጠበቅና የኦፕሬሽን ሥራውን በማቀላጠፍ የኃይል ማመንጫ ጣቢያው የሚጠበቅበትን ኃይል በአግባቡ እንዲያመርት ከማድረጉም ባሻገር በታችኛው ተፋሰስ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል መሆኑንም አቶ ያፌት ገልጸዋል፡፡
በግድቡ አካላት ላይ ከሚከናወኑ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች በተጨማሪ በግድቡ ሠው ሰራሽ ሀይቅ ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኝውን የእንቦጭ አረም ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ለማስወገድ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፍ መልኩ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የቆቃ የውኃ ኃይል ማመንጫ ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



