የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የሁለተኛው ምዕራፍ ሳፕ ትራቭል ማኔጅመንት ሞጁል ስልጠና መሰጠት መጀመሩን በተቋሙ የሰው ኃይል ስልጠናና ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ባትሪ ደረሰ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባሉ የተለያዩ ኃይል ማመንጫዎችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚመደቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ቴክኒሺያኖች ስልጠና መሰጠት ጀምሯል፡፡
ለአራት ወራት በሚቆየው ስልጠና ላይ 77 ሰልጣኞች ተካተው በሶስት የተለያዩ ቦታዎች ማለትም በኮተቤ ማሰልጠኛ፣ በአዳማ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እና እና በአዳማ ማከፋፈያ ጣቢያ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ከሰልጣኞቹ መካከል 56 የሚሆኑት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተመለመሉ አዲስ ሰልጣኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 21 ሰልጣኞች ደግሞ ከድርጅቱ ሰራተኞች መካከል ትምህርታቸውን በማሻሻላቸው ለስልጠናው የተመለመሉ መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሮ ሜካኒል ስልጠናው የድርጅቱን የሰው ኃይል ክፍተት በመሙላት ዓይነተኛ ሚና ሲወጣ መቆየቱን የገለፁት አቶ ባትሪ ከድርጅቱ ማሰልጠኛ ማዕከል በኤሌክትሮ ሜካኒካል ሰልጠነው ለከፍተኛ ኃላፊነት የበቁ የተቋሙ ሰራተኞች መኖራቸውን አስታውሰዋል፡፡
በዚህኛው ዙር ስልጠና ከአርብቶ አደር አካባቢ ለተመለመሉ ሰልጣኞች ልዩ ድጋፍ የሚያገኙበት አቅጣጫ ተቀምጦ በሥራ ላይ መዋሉንም ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ባትሪ ገለፃ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስልጠናውን ይዘትና የስልጠና አሰጣጡን ለማሻሻል የሚያስችሉ ጥረቶች ተጀምረዋል፡፡
አሁን በተጀመረው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስልጠና ላይ ቀጣይነት ያለው የሰልጣኞች ምዘና ሥርዓትን (Continuous assessment) እንዲሁም ሰልጣኞች ከቴክኒካል ዕውቀት በተጨማሪ ባህሪያዊ እሴቶችን (Behavioral values) የሚጨብጡበት መርሃግብሮች ተካተው እንደሚሰጡ ገልፀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የሳፕ ምዕራፍ ሁለት ትግበራ ውስጥ ከተካተቱት ሞጁሎች ውስጥ የትራቭል ማኔጅመንት የተጠቃሚዎች ስልጠና በይፋ መጀመሩን አቶ ባትሪ ተናግረዋል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ የሚተገበረው የትራቭል ማኔጅመንት ሞጁል በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ያለውን የአበል አከፋፈል ሥርዓት በማዘመን ከማዕከል ሆኖ ቁጥጥር ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
ስልጠናው በተግባርና በንድፈ ሀሳብ ታግዞ እንደሚሰጥ የገለጹት ኃላፊው በሥልጠናው ላይ ከሁሉም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና ሪጅኖች የተውጣጡ የፋይናንስ ባለሙያዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ለሳፕ ምዕራፍ ሁለት የሞጁል ስልጠና 50 ኮምፒዩተሮች ያሉት የኮምፒውተር ስልጠና ማዕከል መቋቋሙን ገልፀዋል፡፡
የስልጠና ማዕከሉ የሚጠበቅበትን ተግባር በበለጠ እንዲወጣ የተለየ ክለላ(Zoning) ኖሮት ከተሽርካሪና ከእግረኛ ማቋረጫነት ተጠብቆ እንዲደራጅ የሚመለከተው አካል ሁሉ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”






