በሁመራ እና አካባቢው የተቋረጠውን ኃይል መልሶ ለማገናኘት የሚያስችል ሥራ ተጀምሯል

በሁመራ እና አካባቢው የተቋረጠውን ኃይል መልሶ ለማገናኘት የሚያስችል ሥራ ተጀምሯል

ከሽሬ- ሁመራ በተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ በደረሰ ተፈጥሯዊ አደጋ ኃይል መቋረጡን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ውበት አቤ እንዳስታወቁት የኃይል ተሸካሚ ምሰሶው የወደቀው  ከሁመራ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እንድሪያስ ቀበሌ ነው።

በዚህም የተነሳ ሁመራ ከተማን ጨምሮ በዳንሻ፣ ባዕከር፣ አዲረመጥ፣ ሶረቃ፣ ማይካድራ፣ አብደራፊ፣ አብርሃጅራ፣ አዲጎሹ እና አደባይ እንዲሁም በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ከሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ተናግረዋል።

የወደቀውን አንድ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ለመጠገን የቴክኒክ ቡድን በሥፍራው ደርሶ ጥገና መጀመሩን የገለፁት ዳይሬክተሩ ጥገናውን ለማጠናቀቅ እስከ አስር ቀናት ሊፈጅ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ የደረሰው ጉዳት እስኪጠገን ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቅም ነው አቶ ውበት ጥሪ ያቀረቡት።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top